Homeዜናና ወቅታዊዜናበዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ከእስያ ሀገራት የተነሱ ምዕመናን ከፍተኛውን ቁጥር...

በዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ከእስያ ሀገራት የተነሱ ምዕመናን ከፍተኛውን ቁጥር አስመዘገቡ

የሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር በ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ላይ የተሳተፉ ምዕመናንን አሐዝ ይፋ አደረገ፡፡ ሚኒስቴሩ ይፋ ባደረገው አሐዝ፣ በሐጅ ሥነ ሥርዐቱ ላይ ከተሳተፉ መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከእስያ ሀገራት የተነሱ ምዕመናን ናቸው፡፡

የሀገሪቱ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ዛሬ ይፋ ባደረገው አሐዝ መሠረት፤ በዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ከመላው ዓለም 1 ሚሊዮን 833 ሺሕ 164 ምዕመናን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ይፋ የተደረገው መረጃ ከአጠቃላይ ተሳታፊ ምዕመናን በተጨማሪ ምዕመናኑ የተነሱበት አሕጉር፣ ሳዑዲ ዐረቢያ ለመድረስ የተጠቀሙበት የትራንስፖርት አማራጭ እንዲሁም የፆታ ተዋፅኦ የተካተተበት ነው፡፡

በዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ላይ ከተሳተፉት መካከል 1 ሚሊዮን 611 ሺሕ 310 ምዕመናን ከሳዑዲ ዐረቢያ ውጪ ካሉ ሀገራት መካ ከተማ የገቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 221 ሺሕ 854 ነዋሪነታቸው በሳዑዲ ዐረቢያ ነው፡፡ በሐጅ ሥነ ሥርዐቱ ላይ 52.27 በመቶውን ቁጥር ያስመዘገቡት ወንዶች ናቸው፡፡ የሴት ምዕመናን ቁጥር 47.73 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በክንውኑ ላይ ከተሳተፉት መካከል 1 ሚሊዮን 546 ሺሕ 345 ምዕመናን ሳዑዲ ዐረቢያ የደረሱት በአውሮፕላን ተሳፍረው ነው የተባለ ሲሆን፣ 60 ሺሕ 251 ምዕመናን በየብስ እንዲሁም 4 ሺሕ 714 ምዕመናን ደግሞ በባሕር አቋርጠው መካ ደርሰው የሐጅ ሥርዐቱን ፈጽመዋል፡፡

ከሑጃጅ መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከእስያ አሕጉር የተነሱት መሆናቸውን ያመለከተው የሳዑዲ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር፣ 22.3 በመቶዎቹ ከዐረብ ሀገራት፣ ከአፍሪካ 11.3 በመቶ፤ ከአውሮፓ፣ ሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም አውስትራሊያ የተነሱት 3.2 በመቶ መሆናቸውን ገልጧል፡፡

የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን መጠናቀቁን ተከትሎ ምዕመናን ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ በሥነ ሥርዐቱ ላይ ለመሳተፍ 12 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ አቅንተዋል፡፡ ሚንበር ቲቪ ትናንት ሰኔ 24/2016 ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኃላፊዎች እንደሰማው እስካሁን ድረስ 4 ሺሕ 600 ምዕመናን ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል፡፡  

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular