በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ተገልጋዮች እርካታ፣ ግንዛቤ እና አመለካከት ዙሪያ በተጠና ጥናት ይፋ ተደረገ፡፡ በሥርዓቱ 12 ሚሊዮን አባወራ እና እማወራዎች ተጠቃሚ ሆነዋል ተብሏል፡፡
በስምንት ክልሎች የተካሄደውን ጥናት ያቀረቡት በአገልግሎቱ የፈንድ ሥጋት እና የኢንቨስትመንት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አዳሙ ወንድምተካ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችን አሐዝ ይፋ አድርገዋል፡፡
12 ሚሊዮን አባወራ እና እማወራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ያመለከተው ጥናት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገልጋዮች እርካታ 68 በመቶ መድረሱን በመጠቆም፣ ከፍተኛ እና ዝቅተኛ እርካታ የተመዘገበባቸውን ክልሎች ተጠቁሞበታል፡፡ ዝቅተኛው የተገልጋዮች እርካታ በደቡብ ክልል ሲመዘገብ፣ ከፍተኛው የተገልጋዮች እርካታ ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስለመሆኑ ጥናቱ ያመለክታል፡፡
በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ዘንድ እርካታ ዝቅ እንዲል ካደረጉት መካከል የመድኃኒት አቅርቦት እና የላቦራቶሪ አገልግሎቶች መሆናቸውን ጥናቱ ጠቅሷል፡፡
በዚሁ ጥናት ላይ በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ግንዛቤ በሀገር አቀፍ ደረጃ 63 በመቶ እንደሆነም በጥናቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ስለ አገልግሎቱ ከፍተኛ ግንዛቤ የተመዘገበው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች መሆኑ ሲጠቀስ፣ ዝቅተኛ ግንዛቤ ያስመዘገቡት አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ናቸው፡፡
ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት፣ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን፣ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎ የሚሠራ ነው፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢ- መደበኛ ኢኮኖሚ የሚሠሩ ወይም መደበኛ ደመወዝና ገቢ የሌላቸው ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ማኅበራዊ የጤና መድኅን ግን በመደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሠማሩትን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ነው፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት የሙከራ ትግበራውን የጀመረው በ2013 በሦስት ወረዳዎች ነበር።
በመላ ኢትዮጵያ የጤና መድኅን ምዝገባና ዕድሳት የሚከናወነው በየዓመቱ ከመስከረም 1 ቀን እስከ የካቲት 30 ቀን ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ነው፡፡ በእነዚህ ወራት እያንዳንዱ ወረዳ ኅብረተሰቡ ገቢ ያገኝባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን ሁለት ወራት መርጦ ምዝገባና ዕድሳት እንዲያካሂድ ያደርጋል፡፡ በዚህ መልኩ የሚከናወነው ምዝገባና ዕድሳት የካቲት 30 ቀን መጠናቀቅ እንደሚኖርበት የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት መረጃ ያመለክታል፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ በሚጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የጤና መድኅን 1 ሺሕ 52 ወረዳዎችን በመሸፈን ከ56 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን መረጃዎች ያሳያሉ።












