ዓለም አቀፉ የሐላል ግብዓት ገበያ በቀጣይ ስምንት ዓመታት የሠላሳ ቢሊዮን ዶላር ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ጥናት አመለከተ፡፡ አዲሱ ጥናት እ.አ.አ በ2032 ዓለም አቀፉ የሐላል ግብዓት ገበያ 89.02 ቢሊዮን ዶላር አንደሚደርስ ግምቱን አስቀምጧል፡፡
የሐላል ግብዓት ገበያ ግምቱን ጥናት ይፋ ያደረገው፤ ‘ቫልዩ ማርኬት ሪሠርች’ የተሰኘ የጥናት እና የምርምር ድርጅት ነው፡፡ የማርኬት ሪሠርች ጥናት ያካተተው የሐላል ግብዓት ገበያ ከ2024 እስከ 2032 ሊኖረው የሚችለውን የገበያ ድርሻ ነው፡፡
ጥናቱ ወቅታዊው ዓለም አቀፍ የሐላል ግብዓት ድርሻው 60.11 ቢሊዮን መሆኑን በመጠቆም፤ በቀጣይ ዓመታት ሊመዘገብ ይችላል ያለውን ዕድገት በአሐዝ አስቀምጧል፡፡ የሐላል ግብዓት ገበያ በቀጣይ ስምንት ዓመታት የ4.46 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሏል፡፡
የሐላል ግብዓት ገበያ በምግብ፣ መድኃኒት፣ መዋቢያዎችን የሚያካትት ነው፡፡ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየጊዜው እየጨመረ የሚገኘው የሙስሊሞች ቁጥር እንዲሁም በሐላል ኢንዱስትሪ ዙርያ ያለው ግንዛቤ በተመሳሳይ ዕድገት በማስመዝገቡና ለምርቶች የሚሰጠው የሐላል ሠርተፍኬት ጥያቄ መበርከቱ፣ የሐላል ግብዓት ገበያው ጎን ለጎን የፍላጎቱን መጠን ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡
የሐላል ግብዓቶች በምግብ፣ መድኃኒት እና መዋቢያ የእስልምና አስተምሕሮ እና ሕግጋትን መሠረት የተዘጋጁትን የሚያቅፍ ነው፡፡ የግብዓቶቹ ምዘና የሐላል መሥፈርትን ለማለፍ በእስልምና አስተምሕሮ መሠረት ከክልከላ ነጻ የሆኑ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በሐላል ኢንዱስትሪ ውስጥ የሐላል ምዘና ሠርተፍኬት የሚሰጡ ድርጅቶች በምግብ እና መዋቢያዎች ውስጥ በእስልምና ክልከላ የተጣለባቸው እንደ አልኮል እና የአሳማ ሥጋ እንዲሁም ሌሎች የተከለከሉ ነገሮች በንጥረ ነገር ደረጃ አለመግባቱን አጣርተው ማረጋገጫ የመስጠት ኃላፊነት ይወስዳሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እያደገ መሆኑ የሚነገርለት ዓለም አቀፉ የሐላል ገበያ፣ 2.3 ትሪሊዮን ዶላር ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ነው፡፡ ገበያው እ.አ.አ በ2025 2.5 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












