Homeዜናና ወቅታዊዜናበአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ቤተ እምነቶች ከታክስ ሙሉ ለሙሉ ነፃ...

በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ቤተ እምነቶች ከታክስ ሙሉ ለሙሉ ነፃ አይሆኑም ተባለ




ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ፣ ቤተ እምነቶች ከታክስ ሙሉ ለሙሉ ነፃ እንደማይደረጉ ተገለጸ፡፡ ምክር ቤቱ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ቤተ እምነቶች ከታክስ ነፃ የማይደረጉባቸውን አማራጮች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

የቤተ እምነቶቹ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የመደረግ አልያም አለመደረግ ጉዳይ የተነሳው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ሰኔ 12/2016 ባካሔደው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

በዚሁ ወቅት የሃይማኖት ድርጅቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ ከግሉ ንግድ ዘርፍ ጋር ተወዳዳሪ ሆነው በሚሠሯቸው በሆቴል ንግድ ሥራ ዘርፍ እና ሕንጻ አከራይተው ገቢ በሚያገኙባቸው ሥራዎች ላይ ተገቢውን ግብርና ታክስ መክፈል ይገባቸዋል ተብሏል፡፡


በመድረኩ ላይ ስለ ቤተ እምነቶች የተነሳው የኢትዮ ቴሌኮም ተወካይ ከቤተ እምነቶች የሚከራዩዋቸውን ቤቶች አስመልክቶ ቤተ እምነቶቹ የንግድ ፍቃድ ስለሌላቸው ሥርዓቱን ተከትሎ ለመሥራት መቸገራቸውን ከገለጹ በኋላ ነው፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሮቤል ታረቀኝ ይህንኑ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት በገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች መምርያ ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ተወዳጅ ሙሐመድ፣ ቤተ እምነቶች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ አለመደረጋቸውን በመግለጽ፣ ከታክሱ ነፃ የሚደረጉት ከእምነት አገልግሎቱ ጋር በቀጥታ የሚገናኙት ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። ሆኖም ቤተ እምነቶቹ ሕንጻ ገንብተው ሱቅ የሚያከራዩ ከሆነ ግን ከታክሱ ነፃ እንደማይሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በምክር ቤቱ መድረክ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሀገሪቱ የምትሰበስበው ታክስ ለጠቅላላ ምርቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ በመሆኑ መንግሥት በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ዓመታት ይህን ለማስተካከል እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ኢዮብ (ዶ/ር) ይህን ለማሳካት የታክስ ፖሊሲዎችን ማስተካከል፣ አዳዲስ የታክስ ፖሊሲዎችን መቅረፅ እንዲሁም የታክስ አስተዳደሩን ማዘመን እንደሚገባና ለዚህም ረቂቅ አዋጁ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።


ሚኒስትር ዲኤታው በጥናት የተገኘው የተጨማሪ እሴት ታክስ የክፍያ ምጣኔውን መጨመር ነው በማለት ‹‹አላስፈላጊ በሆነ ምክንያት ከታክስ ነፃ የተደረጉት ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ወስነናል›› ሲሉ መናገራቸውንም የሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል፡፡


በኢትዮጵያ በሃይማኖት ተቋማት የሚሰጡት የእምነት ወይም ከአምልኮት ጋር የሚገናኙ አገልግሎቶች ከማንኛውም ታክስ ነፃ እንደሆኑ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የገቢ ግብር አዋጅ ላይ ሠፍሯል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular