Homeዜናና ወቅታዊዜናበግል ከሐጅ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን የበረራ መስተጓጎል ገጥሟቸዋል ተባለ

በግል ከሐጅ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን የበረራ መስተጓጎል ገጥሟቸዋል ተባለ

ከሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን በግል ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱ ኢትዮያውያን የበረራ መስተጓጎል እንደገጠማቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ፡፡ ምክር ቤቱ የበረራ መስተጓጎል ገጥሟቸዋል ያላቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር 93 ነው፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ ሰኔ 17/2016 እንዳስታወቀው፣ የበረራ መስተጓጎል የገጠማቸው ሑጃጅ በግል ትኬት የቆረጡ ናቸው ብሏል፡፡ የምዕመናኑ በረራ የተስተጓጎለው ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ሲገቡ ፓስፖርታቸውን የተቀበላቸው ኩባንያ በሰዓቱ ደርሶ ፓስፖርታቸውን ባለመመለሱ ሳቢያ መሆኑም ተገልጧል፡፡

ከፓስፖርት በተጨማሪም ለበረራ መስተጓጎሉ ምክንያት ሆነዋል ያላቸውን ጉዳዮች ዘርዝሯል፡፡ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች ውስጥ ከመካ ወደ ጂዳ ከተማ የሚወስዳቸው አውቶብስ ዘግይቶ መምጣት፣ የሑጃጅ በሰዓቱ ተጠቃልለው ወደ አውቶብሱ አለመግባት፣ የግል ተመላሽ ሑጃጅ የትኬት መረጃ በሑጃጅ መስተንግዶ ሲስተም ውስጥ የሚገኝ ባለመሆኑ መረጃውን ከተመላሾቹ ወስዶ ለማስተካከል የወሰደው ጊዜ ይገኝበታል፡፡

የመልስ ጉዟቸው ለተስተጓጎለባቸው የሐጅ ተመላሾች የእስልምና ጉዳዮ ጠቅላይ ምክር ቤት በጂዳ ከተማ የመቆያ ሆቴል በመከራየት የመልስ ጉዟቸውን ለማስተካከል አማራጭ እየፈለገ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡

በረራ የተስተጓጎለባቸውን ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ የምክር ቤቱ የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሸይኽ ዓብዱልፈታህ ሙሐመድ፣ ምዕመናኑን በተቻለ ፍጥነት ተለዋጭ በረራ እንዲያገኙ ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል ጋር በመገናኘት ለችግሩ መፍትሔ በማፈላለግ ላይ ነን ማለታቸው ተመላክቷል፡፡

ለ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የተጓዙ ምዕመናን ቁጥር 12 ሺሕ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

ሥነ ሥርዐቱን ለመከወን ወደ ቅዱሳኑ ከተሞች መካ እና መዲና ከተጓዙት ውስጥ 5 ምዕመናን ሕይወታቸው ማለፉን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular