Homeዜናና ወቅታዊዜናከ1 ሺሕ 300 በላይ ምዕመናን በሐጅ ወቅት ሕይወታቸው ማለፉን የሳዑዲ ዐረቢያ ጤና...

ከ1 ሺሕ 300 በላይ ምዕመናን በሐጅ ወቅት ሕይወታቸው ማለፉን የሳዑዲ ዐረቢያ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

በዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ወቅት ከ1 ሺሕ 300 በላይ ምዕመናን መሞታቸውን የሳዑዲ ዐረቢያ ጤና ሚኒስቴር በዛሬው እለት አስታወቀ። ኅልፈታቸው ከተሰማው ምዕመናን ውስጥ 83 በመቶ የሚሆኑት የሐጅ ቪዛ ያልተሰጣቸው መሆናቸው ተገልጿል።

የሳዑዲ ዐረቢያ ጤና ሚኒስቴር ዛሬ እሑድ ሰኔ 16/2016 ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ የሟቾቹ አሐዝ 1 ሺሕ 301 መድረሱን አረጋግጧል።

የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ለበርካታ ምዕመናን ኅልፈት ምክንያት የሆነው ረዥም ርቀት በፀሓይ ንዳድ መጓዛቸው ነው።

ሳዑዲ ዐረቢያ በዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለተሳተፉ ምዕመናን እንደ ቀዳሚዎቹ ዓመታት ሁሉ የተለየ ቪዛ አዘጋጅታ እንደነበር የሚታወቅ ነው። በዚሁ መሠረት በተለይ የሐጅ ቪዛ ያልተሰጣቸው ምዕመናን መካ ከተማ እንዳይገቡ ክልከላ አስቀምጣ ነበር።

ሀገሪቱ ያለ ሐጅ ቪዛ በመካ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ምዕመናን ላይ ቅጣት እንደምትጥል ቀደም ብላ ያስታወቀች ሲሆን፣ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንንም ከከተማ እንዲወጡ ማድረጓ ይታወሳል።

የጤና ሚኒስቴር በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ከሟቾቹ አሐዝ 83 በመቶው ለሐጅ ምዝገባ ያላደረጉ መሆናቸውንም አስታውቋል።

በተጠናቀቀው ሳምንት በወጡ መረጃዎች በሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ወቅት ሕይወታቸው ካለፈ ምዕመናን ውስጥ በርካቶቹ ግብፃዊያን መሆናቸው ሲነገር ነበር።

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular