ሐጅ ሆነ!

ዛሬ ጁመዓ ሐጅ በይፋ ተጀምሯል፡፡ ሑጃጆች “የውም አት ተርዊየህ” ላይ ተገኝተዋል። ሚና ደርሰው ለማደርም ተንቀሳቅሰዋል። እንግዶቹን የምታስተናግደው ሳዑዲ ዐረቢያ ባወጣችው መረጃ መሠረት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናንን ከመላው ዓለም ተቀብላለች፡፡

አልጋ ወራሹ ሙሐመድ ቢን ሰልማንም ሀገራቸው የአላህ እንግዶችን እያስተናገደች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ በቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ መሳተፍ ቢኖርባቸውም ሳይሄዱ እንደቀሩ የሳዑዲ ዐረቢያ መገናኛ ብዙኃን ጽፈዋል፡፡ ጋዜጦቹ ቢን ሰልማን ለጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኔ ‘ከሑጃጆች ጋር በተገናኘ መምጣት አልችልም’ በማለት ይቅርታ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውን ነው ያስነበቡት፡፡

የቢን ሰልማን ሳዑዲ በዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ እንዲሳተፉ 2 ሺሕ የፍልስጤማዊያን ሰማዕታት ቤተሰቦችን ጋብዛለች፡፡ አንድ ሺሕ ፍልስጤማዊያን ቀድመው ገብተዋል፡፡

ዐብዱል ሐሚድ ለሐጅ ከታደሉት መካከል ነው፡፡ ዐብዱል ሐሚድ ናሽናል ለተሰኘ መገናኛ ብዙኃን እንዳለው ከሆነ፣ በፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር ውስጥ ሾፌር ሆኖ ይሠራ ነበር፡፡ በሥራው ጠባይ የተነሳ በጋዛ በርካቶች ቦንብ ሲዘንብቸው ተመልክቷል፡፡ የቆሰሉትንም ሆነ የሞቱትን በአምቡላንስ ሸኝቷል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖም ከእነዚህ መሃል ሙሉ ቤተሰቡ ይገኝበታል – ምንም እንኳን በእርሱ አምቡላንስ ወደ ሕክምና ተቋም ባይወሰዱም፡፡

ዐብዱል ሐሚድ ቤተሰቦቹን ወደ ቀጣዩ ዓለም ሸኝቶ እሱ ከሞት መምለጡ እንደሚገርመው ይናገራል፡፡ ለጋዜጠኞች ደጋግሞ “ከሞት የተረፍኩት ሺሕ ጊዜ ነው” የሚለው ለዚሁ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ተርፎ ቅድስቲቱ መካ ከተማ መድረሱን የማይታመን ነው ይላል፡፡ “የመስጂዶቹን ሚናራ ስመለከት ማመን አቅቶኝ ነበር” ብሏል ስሜቱን ሲገልጽ፡፡ ዐብዱል ሐሚድና ቀሪ ሑጃጆች ወደ ሚና የሚያደርጉትን ጉዞ ብርታት ጀምረውታል፡

ለእነ ዐብዱል ሐሚድ እና ሌሎችም ሑጃጆች በዘንድሮው ዓመት ፈተና የሆነው ጉዳይ የሳዑዲ አየር ንብረት መሆኑ ተደጋግሞ እየተነገረ ነው፡፡ በረሐማዋ ሳዑዲ ሐጅ በሚከናወንበት ጊዜ ያስተናገደችው የአየር ጠባይ ከወትሮው ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ በሳዑዲ ዐረቢያ እስካሁን ድረስ የሑጃጆች ሞት የተመዘገበ ቢሆንም፣ በቀጥታ ከሙቀቱ ጋር ግንኙነት ስለመኖሩ ወይም አለመኖሩ ግን ይፋዊ መረጃ አልወጣም፡፡

ባለፈው ዓመት በነበረው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ወቅት በተመዘገበው ከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ 10 ሺሕ የሕመም ኬዞች እንደተመዘገቡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አንዳንድ ሑጃጆች ላይ ሙቀቱ ሞት አስከትሏል፡፡ በርግጥ በቅርብ ዓመታት የሚመዘገበው የሞት ምጣኔ ከ40 ዓመት በፊት ከነበረው በ47.6 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ሙቀቱ ቢበረታም ሑጃጆች ግን እስካሁን ድረስ አልተረቱም፡፡ የሑጃጆቹ ጽናት በቺካጎ ነዋሪው ሻሪቅ ሜሞ ቃል የሚወከል ይመስላል፡፡ ሻሪቅ ለአሶሽየትድ ፕሬስ እንዲህ አለ፡- “አላህ ብርታቱን ይሰጣል”፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular