በአቢሲንያ ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ተዘጋጅቶ በ”ሚንበር ቲቪ” የሚተላለፈው ‘‘አሚን አዋርድ የሥራ ፈጠራ ውድድር”፣ የፊታችን እሑድ ሰኔ 9/2016 በሚከበረው የዒድ አል አድሓ በዓል ዕለት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ባንኩ አስታወቀ፡፡ አቢሲንያ ባንክ በውድድሩ አንደኛ ለሚወጣው ተወዳዳሪ ከፍተኛውን አንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚያበረክት ገልጿል፡፡
የባንኩ ኃላፊዎች ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 6/2016 በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፣ የአሚን አዋርድ ሥራ ፈጠራ ውድድር ፍጻሜ የሚካሔደው በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ነው፡፡
የአቢሲንያ ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ቢዝነስ ሠርቪስ ዳይሬክተር እና “የአሚን አዋርድ 2” የሥራ ፈጠራ ውድድር አዘጋጅ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበጋዝ ይማም በሁለተኛው “አሚን አዋርድ” በቀዳሚነት ከመጡት 180 ተወዳዳሪዎች ውስጥ 126 ተወዳዳሪዎች ሐሳባቸውን ማቅረብ መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ከመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሳተፉት ተወዳዳሪዎች ያቀረቧቸው ሐሳቦች በቴክኖሎጂ ግብዓቶች፣ በግብርና ምርቶች ማሳደጊያ፣ በግንባታ ቴክኖሎጂ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በዶሜስቲክ ትሬድ፣ በሠርቪስ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በትምህርትና ጤና እና በኢ – ኮሜርስ ላይ ያተኮሩ እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡
በዒድ አል አድሓ በዓል እለት በሚካሔደው የፍጻሜ ውድድር ላይ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ለሚያገኙ ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከት ባንኩ አስታውቋል፡፡ ውድድሩን በ1ኛ ደረጃ ደረጃ ለሚያጠናቅቀው ተወዳዳሪ የሚበረከተው የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ አንድ ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ሌሎች ተወዳዳሪዎች እንደ ደረጃቸው ከሁለት መቶ ሺሕ ብር ጀምሮ እንደሚሸለሙ ታውቋል፡፡
አቢሲንያ ባንክ የወለድ ነጻ ባንክ አገልግሎት ሥራውን የጀመረው በታኅሣሥ 2010 ነበር፡፡ ባንኩ የሸሪዐ መርሆችን በጠበቀ መልኩ በተቀማጭ፣ በብድር እና ሌሎች የአገልግሎት አማራጮችን በማቅረብ የደንበኞችን ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ችሏል፡፡

ባንኩ ከ24 ቢሊዮን በላይ የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የግል ባንኮች በቀዳሚነት መቀመጡንም አስታውቋል። አቢሲንያ ባንክ ከ2011 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎቹን ወደ ሥራ በማስገባት በአሁኑ ጊዜ ከ69 በላይ የሚሆኑ ቅርንጫፎች በመላው ኢትዮጵያ ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
አቢሲንያ ባንክ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚል ለሁለት ዙር ያካሔደው የሥራ ፈጠራ ውድድር ላለፉት ወራት በተከታታይ በ”ሚንበር ቲቪ” ሲተላለፍ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
“አሚን አዋርድ” ያገኘው የቴሌቪዥን ሥርጭት አቻ ተቋማት ለመሰል ሥራ ማነሳሳቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ተወዳዳሪዎችም የሥራ ፈጠራቸው በቴሌቭዥን ሥርጭት ሽፋን በማግኘቱ ሐሳባቸውን ለሌሎች ማድረስ ችለው ከተቋማት ጋር በአጋርነት እየሠሩ መሆናቸውን አቢሲንያ ባንክ ባካሔደው የዳሰሳ ጥናት መረዳት መቻሉን በዛሬው እለት አስታውቋል፡፡
የአቢሲንያ ባንክ አሚን አዋርድ የሥራ ፈጠራ ውድድር መድረክ ሲመራ የቆየው በባንኩ ከወለድ ነጻ አገልግሎት ብራንድ አምባሳደር ጋዜጠኛ ሙሐመድ ፈረጅ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












