Homeዜናና ወቅታዊዜናበሀገራዊ ምክክር የተወካዮች ልየታ ወቅት ከተሳትፎ ውጪ መደረጉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና...

በሀገራዊ ምክክር የተወካዮች ልየታ ወቅት ከተሳትፎ ውጪ መደረጉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ገለጸ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ በሀገራዊ ምክክር የተወካዮች ልየታ ወቅት ተሳታፊ አለመደረጉን የገለጸው ለእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ረቡዕ ግንቦት 21/2016 በጻፈው ደብዳቤ፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሠራሩን ካላሻሻለ ዕውቅና አልሰጥም ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የመጣው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ሦስተኛ ያለውን የምክክር ምዕራፍ ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በዐድዋ መታሠቢያ ሙዝየም ባስጀመረውና ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የምክክር መድረክ በቀጣይ በክልሎች የሚካሄድ መሆኑን አስታውቋል፡፡  

በአንጻሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮ ከፍተኛ ምክር ቤት፣ ለሀገራዊ ምክክር በሚደረገዉ ሒደት የመጀመሪያ ዙር የምክክር ጉባዔ የሚሳተፉ ሰዎች ተለይተው ወደ ሥራ እንደገቡ በማስታወስ፣ በተሳታፊ ልየታ ወቅት ተሳትፎ እንዳላደረገ ጠቅሷል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሒደት የክልሉን ሙስሊም በተገቢው መልኩ አሳታፊ እንዲያደርግ ጥሪ የቀረበበት የምክር ቤቱ ደብዳቤ፣ ይህን እንዲያቀርብ የጠየቀው ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ነው፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “አሠራሩን የማያሻሽል ከሆነ” በቀጣይ “ምንም ዐይነት ትብብር” እንደማያደርግና ዕውቅና እንደሚነፍገው አስታውቋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ቅሬታ ሲቀርብበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ግንቦት 12/2016 ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ለአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር እና ለክልሉ ሰላምና ደኅንነት ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ፣ የሀገራዊ ምክክር የተሳታፊ ልየታ አሠራር ሳይሻሻል ባለበት የሚቀጥል ከሆነ ለምክክሩ ዕውቅና እንደማይሰጥ አስጠንቅቆ ነበር፡፡ በምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ጀውሐር ሙሐመድ በተጻፈው ደብዳቤ፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልሉ ባካሄደው ጉባዔ ላይ ያሳተፈው “የኔ የሚለውን ብቻ” እንደሆነ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልል እስልምና ጉዳዮች ከቀረበበት ቅሬታ በፊት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ አካሔዱ ላይ ተቃውሞ ሲያቀርብበት ነበር፡፡ ምክር ቤቱ ይህንኑ ተቃውሞውን ለዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ በጻፈው ደብዳቤ ገልጧል፡፡ ኮሚሽኑ ከምክር ቤቱ ለቀረበበት ተቃውሞ እስካሁን ድረስ የሰጠው ይፋዊ ምላሽ የለም፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት በእስላማዊ ጉዳዮች አተኩረው ከሚሠሩ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች እና አንቂዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ እስካሁን ድረስ በነበረው በዚህ የልየታ ሒደት የሙስሊሞች ውክልና ከ2 በመቶ ያነሰ መሆኑን የሰበሰበውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ጠቅሷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular