እሑድ , ذو الحجة 17, 1445
Google search engine
Homeዜናና ወቅታዊዜናሃይማኖትን አስመልክቶ በሚወጡ ሕጎች የእምነቶች “ልዩ ባሕሪያት እና ድንጋጌዎች” ከግምት ውስጥ እንዲገቡ...

ሃይማኖትን አስመልክቶ በሚወጡ ሕጎች የእምነቶች “ልዩ ባሕሪያት እና ድንጋጌዎች” ከግምት ውስጥ እንዲገቡ ተጠየቀ

የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ሃይማኖትን አስመልክቶ በሚወጡ ሕጎች እና ደንቦች የእምነቶችን “ልዩ ባሕሪያት እና ድንጋጌዎች” በተቻለ መጠን ከግምት ውስጥ እንዲገቡ ጠየቀ። ፓርቲው በኢትዮጵያ አዲስ የተዘጋጀው “የሃይማኖት ጉዳዮች አዋጅ” ከመጽደቁ በፊት የሃይማኖት ተቋማትን እና ዜጎችን አስተያየት እና ስጋት ማካተት እንደሚገባ አሳስቧል።

ፓርቲው ይህን ያለው ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 10/2016 ባወጣው መግለጫ ነው። ነእፓ በመግለጫው ላይ በቅርቡ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ዜጎችን ስጋት እና ጥርጣሬ ውስጥ የጣለ መሆኑን መረዳቱን በመግለጽ በሚመለከታቸው የእምነት ተቋማት “በቂ ውይይት” ሳይደረግበት ሕግ ሆኖ እንዲወጣ የተጣደፈ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁሟል።

ረቂቅ አዋጁ በተለያዩ ቤተ እምነቶች ዘንድ ተቃውሞ ማስነሳቱን የገለፀው የነእፓ መግለጫ፣ ከቤተ እምነቶቹ ውስጥ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንደሚገኝበት ጠቅሷል።

ፓርቲው በመግለጫው አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ሊደረግ ይገባል ያላቸውን ጉዳዮችም ዘርዝሯል። ነእፓ ከዘረዘራቸው መካከል ከሚመለከታቸው የሃይማኖት ተቋማት ጋር ውይይት ማካሄድ፣ በቂ ግብዐት መሰብሰብ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ የሃይማኖት ተቋማቱ እና ጠቅላላ ዜጎች ያሏቸው አስተያየት እና ስጋት በሚገባ እንዲወሰድ አሳስቧል።

ከዚሁ ጋር አያይዞ ፓርቲው ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖተኛነት እና ሃይማኖት ከፍተኛ ዋጋ እና ክብር እንደሚሰጡ በመጠቆም፣ በሀገሪቱ የሚወጡ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና አሠራሮችም በአንዳንድ የአውሮፓ ሀገሮች እንደሚታየው ሃይማኖት የለሽነትን ለማስፋፋት ወይም ሃይማኖቶች በኢትዮጵያውያን ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ከፍተኛ ቦታ እና ክብር የመገደብ ዓላማ ያላቸው እንዳይሆኑ ልዩ ትኩረት ይሰጥበት ብሏል።

በነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ከመፅደቁ በፊት የዜጎች አስተያየት እንዲካተት የተጠየቀበት ረቂቅ አዋጅ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቃውሞ የቀረበበት ነው። ምክር ቤቱ ሚያዝያ 16/2016 ባወጣው መግለጫ፣ አዋጁ “ነባር ችግሮችን ከመቅረፍ ይልቅ የሚያባብሱና ተጨማሪ ችግሮችን የሚያስከትሉ” አንዳንድ ድንጋጌዎች እንዳሉበት መረዳቱን ጠቅሶ ነበር። ምክር ቤቱ ሥጋቱን ያሰፈረበትን ደብዳቤ የጻፈው የሕዝበ ሙስሊምን ፍላጎትና ሥጋት በመጋራት እንደሆነም ገልፆ ነበር።

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments