ለ1445ኛ ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዓት ክንውን የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ሑጃጆች ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 13/2016 ሳዑዲ ዐረቢያ ደረሱ። ሑጃጆቹ ዛሬ ንጋት ላይ ሳዑዲ ዐረቢያ የደረሱት በሳዑዲ አየር መንገድ አውሮፕላን ተጉዘው ነው፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን 12 ሺሕ ኢትዮጵያውያንን መመዝገቡ ይታወቃል። ከእነዚህ ውስጥ ትናንት ንጋት ላይ ባስጀመረው በረራ በአጠቃላይ 312 ሑጃጆችን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ይልካል። ንጋት ላይ ወደ ሳዑዲ ከደረሱት በተጨማሪ 267 ሑጃጆች ረፋድ ላይ ለጉዞ እንደሚነሱ ሚንበር ቲቪ ሰምቷል። እነዚህ ሑጃጆች በረራ የሚያከናውኑት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው።

ለዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ኢትዮጵያውያን ሑጃጆችን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የሚያደርሰው እንደ ቀደመው ጊዜ ሁሉ በዋነኝነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። አየር መንገዱ ሑጃጆችን ብቻ እንደሚያሳፍር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐጅ ኮሚቴ የሲስተም ተጠሪ አቶ አንዋር ሙስጠፋ ከዚህ ቀደም ለሚንበር ቲቪ ገልፀዋል። ለሑጃጆች በሁለተኛነት የበረራ አገልግሎት የሚሰጠው አየር መንገድ፣ የሳዑዲ ዐረቢያው ሳዑዲያ ነው። ከአየር መንገዶቹ ውስጥ ኢትዮጵያ አየር መንገድ 8 ሺሕ ምዕመናንን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የሚያደርስ ሲሆን ቀሪዎቹ ሳዑዲያ ይበራሉ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኢትዮጵያውያን ምዕመናን ሳዑዲ ዐረቢያ ሲደርሱ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ በዛሬው ዕለት ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የበረሩ ኢትዮጵያውያን መዳረሻቸው መዲና ከተማ ይሆናል ተብሏል፡፡ ምክር ቤቱ ሑጃጆቹን የሚልከው እስከ ሰኔ 2/2016 ድረስ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ምዕመናንን ወደ ሐጅ የሚልከው በተመዘገቡበት ቅደም ተከተል የነበረ ሲሆን ይህ አሠራር ምክር ቤቱ አዲስ መተግበር በጀመረው የአካባቢ ሁኔታ፣ ባህር እና ቋንቋን ከግንዛቤ በሚያስገባው “የቡድን” አሠራር እንደተተካ አስታውቋል። በዚሁ መሠረት በዛሬው እለት ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የበረሩት ከምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ የተመዘገቡ ምዕመናን ናቸው።
የ1445ኛ ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ለማከናወን ከመላው ዓለም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለዚሁ ክንውን የመጀመሪያዎች ሑጃጆች ሳዑዲ ዐረቢያ መዲና ከተማ የገቡት ግንቦት 1/2016 ነበር። ለዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ቀድመው መዲና ከተማ የደረሱት የሕንድ ዜጎች ሆነዋል። [ሚንበር ቲቪ]
(ይህ ዜና ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ ዘገባ ታክሎበታል)












