Homeዜናና ወቅታዊዜናየሀገራዊ ምክክር የተሳታፊ ልየታ ባለበት ከቀጠለ ለምክክሩ ዕውቅና እንደማይሰጥ የአማራ ክልል መጅሊስ...

የሀገራዊ ምክክር የተሳታፊ ልየታ ባለበት ከቀጠለ ለምክክሩ ዕውቅና እንደማይሰጥ የአማራ ክልል መጅሊስ አስታወቀ

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የሀገራዊ ምክክር የተሳታፊ ልየታ አሠራር ሳይሻሻል ባለበት የሚቀጥል ከሆነ ለምክክሩ ዕውቅና እንደማይሰጥ በዛሬው እለት አስታወቀ። ምክር ቤቱ በአማራ ክልል ከዕውቅና ውጪ ሙስሊሙን በማግለል ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመጀመሪያ ዙር ጉባዔ ማካሄዱን ገልጿል።

ምክር ቤቱ ይህንኑ ዛሬ ግንቦት 12/2016 ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ለአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር እና ለክልሉ ሰላምና ደኅንነት ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ ላይ አስታውቋል።

በአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ጀውሐር ሙሐመድ በተጻፈው ደብዳቤ፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልሉ ባካሄደው ጉባዔ ላይ ያሳተፈው የኔ የሚለውን ብቻ እንደሆነ ተጠቁሟል።

አካሄዱን የተቸው ምክር ቤቱ፣ ሕዝበ ሙስሊሙን ያገለለ ሀገራዊ ምክክር የሚፈለገውን መልካም ውጤት ያመጣል የሚል እምነት እንደሌለውም አብራርቷል።

ምክር ቤቱ በደብዳቤው፣ አሁን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል እየሄደበት ይገኛል ያለውን አሠራር እንዲያሻሽል ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ የሚያካሄደውን የተሳታፊ አካላት ልየታ በፍትሐዊነት በድጋሚ እንዲቃኝ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥያቄ ቀርቦለት ነበር።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ ኮሚሽኑ በሚያካሄደው ምክክር ላይ የሕዝበ ሙስሊሙ አጀንዳ እንዲካተት፣ የተሳታፊ አካላት ልየታ በፍትሐዊነት በድጋሚ እንዲቃኝ ቢጠይቅም ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አደርገዋለሁ ላለው ምክክር ተወካይ ያስመርጣሉ ተብለው ከተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን እና የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የተገለሉ ኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ዕድሮች እና የንግዱ ማኅበረሰብ ተካተዋል። በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት ተዘለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሳምንት በፊት በእስላማዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ከሚሠሩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች እና አንቂዎች ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ በምክክር ኮሚሽኑ የተሳታፊ አካላት ልየታ የተመረጡ ሙስሊሞች ቁጥር ከ2 በመቶ በታች እንደሆነ ይፋ አድርጓል። [ሚንበር ቲቪ]

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular