የቀንድ ከብት ሐላል ሥጋ ገበያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጣይ ሰባት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት ሊያስመዘግብ እንደሚችል አዲስ ይፋ የተደረገ ጥናት አመለከተ፡፡ ገበያው እ.አ.አ እስከ 2031 ድረስ የ7.8 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ያስመዘግባል የሚል ግምት ተቀምጧል፡፡
የዓለም አቀፉን የሥጋ ገበያ አዲስ ጥናት ይፋ ያደረገው “አስቱት አናሊቲካ” የተሰኘ የግል የጥናት ተቋም ነው፡፡
ተቋሙ በቀንድ ከብት ሥጋ ላይ በተናጠል ባስቀመጠው የጥናት ግምት መሠረት፤ በ2022 እ.አ.አ 162.30 ቢሊዮን ዶላር ያንቀሳቅስ ነበር የተባለው የቀንድ ከብት ሐላል ሥጋ ገበያ፣ ከሰባት ዓመት በኋላ በ2031 295.98 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ አዲሱ ጥናት የሐላል ሥጋ ገበያ ዓመታዊ ዕድገቱ 7.8 ይሆናል ሲል አስፍሯል፡፡
የጥናት ተቋሙ ለዓለም አቀፍ የቀንድ ከብት ሐላል የሥጋ ገበያ ዕድገት ዋንኛ ምክንያት ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች ዘርዝሯል፡፡ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙስሊሙ ቁጥር መጨመር እንዲሁም ስለ ሐላል መመዘኛዎች ያለው የግንዛቤ መስፋፋት ተጠቃሽ ነው፡፡ ሐላል ምርቶች ከሙስሊሙ ውጪ ባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዕውቅና እያተረፉ መምጣታቸውም በምክንያትነት ሠፍሯል፡፡
በቀጣይ ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘግባል የተባለው ዓለም አቀፉ የቀንድ ከብት ሐላል ሥጋ ገበያ፣ በሥነ ምግባር መለኪያ እንዲሁም ሥጋውን ለገበያ ከማቅረቡ በፊት ከሚያሳልፍበት ሒደት አንጻር በአሁኑ ወቅት በጤና ረገድ ተመራጭ እየሆነ መምጣቱ በሥፋት ይነገራል፡፡
የጥናት ተቋሙ ካስቀመጠው የቀንድ ከብት ሥጋ ውጪ ዓለም አቀፉ አጠቃላይ የሐላል ሥጋ ገበያ፣ በ2022 810.4 ቢሊዮን ዶላር ግምት ተቀምጦለት ነበር፡፡
በእስልምና አስተምህሮ መሠረት የእንስሳት እርድ በሚፈጸምበት ወቅት፣ ለምግብነት ሐላል (የተፈቀደ) ለመሆን የተቀመጠውን መሥፈርት እንዲያሟላ ይጠበቃል፡፡ ከመሥፈርቶች ውስጥ ስለት ያለው መሣሪያ መጠቀም፣ ለእርድ የሚቀርበው እንስሳ ጤናማ አቋም ላይ መገኘት እንዲሁም በአላህ (ሱ.ወ) ሥም መታረዱ ይጠቀሳል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሐላል ሥጋ በማቅረብ በቀዳሚው ረድፍ ላይ የተቀመጠችው ብራዚል ነች፡፡ ብራዚል ለእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል ሀገራት ብቻ 14.04 ሊዮን ዶላር የሚገመት ሐላል ሥጋ ታቀርባለች፡፡
የሐላል ሥጋ አቅርቦት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ የሚገኘው ሐላል ኢንዱስትሪ አንደኛው ዘርፍ ነው፡፡ ሰባት ዘርፎችን የሚያቅፈው ይህ ኢንዱስትሪ፤ በሥሩ ምግብን ጨምሮ እስላማዊ ፋይናንስ፣ ሐላል ቱሪዝም፣ ሐላል ፋሽን፣ ሐላል ሚዲያ እና መዝናኛ፣ የመድኃኒት እና ሐላል መዋቢያዎችን ያካትታል።
በሐላል ኢንዱስትሪ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ በምትይዘው ኢትዮጵያም፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐልል ሠርተፍኬት እንደሚሰጥ ይናገራል። በተመሳሳይ የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትም እንዲሁ ከእርድ ጋር በተገናኘ ለበርካታ ዓመታት እውቅና ሲሰጥ ቆይቷል። በግሉ ዘርፍ ላለፉት አራት ዓመታት እውቅና እየሰጠ የሚገኘው “ኢትሴፍ” የተሰኘ ድርጅት ሲሆን፣ በነሐሴ 2014 በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሐላል ምግብና ቱሪዝም አውደ ርዕይና ጉባዔ አዘጋጅቶ ነበር። ድርጅቱ ከምግብ ጋር በተገናኘ የሐላል ሠርተፍኬት የሚሰጥ ነው። [ሚንበር ቲቪ]












