Homeዜናና ወቅታዊዜናበሀገራዊ ምክክር የሙስሊሞች ውክልና አናሳ መሆኑን መጅሊስ አስታወቀ

በሀገራዊ ምክክር የሙስሊሞች ውክልና አናሳ መሆኑን መጅሊስ አስታወቀ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) በኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን ሒደት የሙስሊሞች ውክልና አናሳ ነው በማለት ቅሬታ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አስታወቀ። ምክር ቤቱ በሀገራዊ ምክክር ዙርያ በእስላማዊ ጉዳዮች አተኩረው ከሚሠሩ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች እና አንቂዎች ጋር በዛሬው እለት ውይይት አካሄዷል።

መጅሊስ ዛሬ እሑድ ግንቦት 4/2016 ከመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች እና አንቂዎች ጋር በአዲስ አበባ ስቴይ ኢዚ ሆቴል ባካሄደው ውይይት ላይ፣ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሒደት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄዎችን በመለየት ለኮሚሽኑ ማቅረቡንም ገልጿል። ምክር ቤቱ የወከላቸው ባለሞያዎች በመድረኩ ላይ እንዳቀረቡት ከሆነ የተለዩት ጥያቄዎች 47 ናቸው።

ጥያቄዎቹ መጅሊስ ባቋቋመው ቴክኒካዊ ኮሚቴ በኩል ተለይተው መቅረባቸውን የገለፀው ምክር ቤቱ፣ ጥያቄዎቹን የመለየቱን ሥራ ቢያጠናቅቅም በሀገራዊ ኮሚሽን ሒደት ተስተውለዋል ባላቸው ችግሮች ዙርያም ማብራሪያ ሰጥቷል።

ምክር ቤቱ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በተመለከተ ባዋቀረው ንዑስ ኮሚቴ ውስጥ የሚገኙ ባለሞያዎች እንደገለፁት፣ በሒደቱ በዋነኝነት የተለየው ጉዳይ ከውክልና ጋር የተገናኘ ነው። ይህ የውክልና ጉዳይ ከኮሚሽኑ ምሥረታ አንስቶ የተስተዋለ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን በቀጣይ በተለያዩ አካላት በተካሄደው ተወካይ መረጣ ወቅት እንደቀጠለ ተገልጿል።

ምክር ቤቱ በምክክር ኮሚሽኑ ተወካይ መረጣ ሒደት የሙስሊሞች ቁጥር አናሳ መሆኑን ከሰባት ወራት በፊት ለኮሚሽኑ መቅረቡን በዛሬው መድረክ ላይ አስታውቋል። ሆኖም እስካሁን ድረስ ምላሽ እንዳልተሰጠው ነው የገለፀው።

በኢትዮጵያ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ውይይት ለማካሄድ በሒደት ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በታኅሣሥ 2014 በጸደቀ የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች፣ በመንግሥት እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮችን እንደሚለይ አሥፍሯል።

ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡለትን እነዚህን አጀንዳዎች ካደራጀ በኋላ ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የመለየት ሚና በአዋጁ ተሰጥቶታል። ተወካይ ያስመርጣሉ ተብለው ከተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን እና የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የተገለሉ ኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ዕድሮች እና የንግዱ ማኅበረሰብ ተካተዋል። በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት እንዳልተካተቱ በዛሬው መድረክ ተጠቁሟል።

እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች እያንዳንዳቸው በየወረዳቸው 50 ተወካዮችን ከመረጡ በኋላ ለልየታ ወደ የዞን ማዕከላት እንደሚልኩ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም አሳውቋል።

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular