ዓለም አቀፉ የሐላል ቱሪዝም ጉባዔ በቱርክ መዲና ኢዝሚር ለሦስተኛ ጊዜ ተከናወነ፡፡ በጉባዔው ላይ ከተለያዩ ዓለም ሀገራት የተውጣጡ የዘርፉ መሪዎች፣ ምሁራን እና ባለሞያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ለሦስት ቀናት የተከናወነው ጉባዔ የተዘጋጀው፤ እንደ ማሌዥያ፣ ኢንዶኔዥያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሐላል ቱሪዝም መዳረሻ ናት በምትባለዋ የቱርክ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትብብር ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ዐርብ በነበረው የጉባዔው ቀዳሚ ቀን ውሎ፣ ከቱሪዝም ዘርፍ የተውጣጡ የ16 ሀገራት ተወካዮች ንግግር የተደመጠ ሲሆን በማግሥቱ ደግሞ የጥናት ውጤቶች ቀርበዋል፡፡ ሦስተኛውን ቀን ጨምሮ የተካሄደው ጉባዔ ዋና ዓላማ፣ በዘርፍ ላይ ግንዛቤ ለማስፋት መሆኑን የአዘጋጇ ሀገር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ጉባዔው ከ40 ሀገራት የተወከሉ 300 ተሳታፊዎችን ያስተናገደ ነው፡፡
ሐላል ቱሪዝም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ተጽዕኖው እየጎላ የመጣው የሐላል ኢንዱስትሪ አንደኛው ዘርፍ ነው፡፡ ሰባት ዘርፎችን የሚያቅፈው ይህ ኢንዱስትሪ፤ በሥሩ ቱሪዝምን ጨምሮ እስላማዊ ፋይናንስ፣ ሐላል ምግብ፣ ሐላል ፋሽን፣ ሐላል ሚዲያ እና መዝናኛ፣ የመድኃኒት እና ሐላል መዋቢያዎችን ያካትታል።
በሐላል ቱሪዝም ዘርፍ በሚታቀፉ ሆቴሎች ውስጥ አልኮል አይሸጥም፡፡ በተጨማሪም ወንዶች እና ሴቶች የዋና እና የስፓ አገልግሎት ሲያገኙ በተናጠል ይሆናል፡፡ ለደንበኞቻቸው ሐላል ምግብ ብቻ የሚያቀርቡት ሆቴሎቹ፣ በአልጋ ክፍል እና በግቢ ውስጥ የመስገጃ ሥፍራዎችን ያሟሉ ናቸው፡፡












