የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባ አዲሱን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ። ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያፀደቀው ማክሰኞ ግንቦት 6/2016 ነው።
ረቂቅ አዋጁ የአርሶ አደር፣ አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ አገሪቱ ከደረሰችበት ዘርፈ ብዙ እድገት ጋር እኩል ለማራመድ ያስችላል ተብሏል።
በተጨማሪም የገጠር መሬት ምዝገባ መረጃን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማደራጀትና ለተጠቃሚው በአግባቡ ለማሠራጨት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በመፍጠር መንግስት እና የመሬት ተጠቃሚዎች አስተማማኝ የሆነ መረጃ የሚያገኙበትን ዘመናዊ የመሬት መረጃ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ የወጣ መሆኑን በዛሬው የምክር ቤት ውሎ ተገልጿል።
ረቂቅ አዋጁ የተፈጥሮ ሐብቶችን በዘላቂነት በመጠበቅና በማልማት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ፣ የሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ማረጋገጥና አካታች ሥርዓት መደንገግ አስፈላጊ መሆኑን የግብር እና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1324/2016 አድርጎ አፅድቆታል፡፡












