በአሜሪካ ጦር ውስጥ በሚገኘው የመከላከያ የስለላ መሥሪያ ቤት የሚሠራው ሐሪሰን ማን፣ ሀገሩ በጋዛ ንጹሐን ላይ ጭፍጨፋ እየፈጸመች ለምትገኘው እስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ በመቃወም ሥራውን ለቀቀ፡፡ የጦር መኮንኑ ሐሪሰን ማን በሊንክድኢን ባሠራጨው መልቀቂያ ላይ፣ ሥራው ለንጹሐን ፍልስጤማዊያን ግድያ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው በሚል ጭንቀት ውስጥ እንደከተተው ገልጧል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ የስለላ መሥሪያ ቤት ሥራ በቃኝ ያለው የጦር መኮንን፣ መልቀቂያ እስካስገባበት ጊዜ ድረስ በመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ ክፍል ውስጥ ተንታኝ ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ዋሽንግተን ፖስት የሐሪሰን ማንን መልቀቂያ በተመለከተ ለአሜሪካ ጦር ቃል አቀባይ ጥያቄ አቅርቤ፣ የመልቀቂያውን ትክክለኛነት አረጋግጠውልኛል ብሏል፡፡ እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ፣ የጦር መኮንኑ የመልቀቂያ ጥያቄ የቀረበው ከ5 ወር በፊት በኅዳር ወር ነው፡፡
ሐሪሰን ማን በመለቀቂያው ላይ እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ከጀመረች አንስቶ ከበርካታ ዘግናኝ ምስሎች ጋር ፊት ለፊት መጋፈጡን በመጥቀስ፣ “ሥራዬን እና ምሥሎቹን ማስታረቅ ከበደኝ” ብሏል፡፡ ሐሪሰን በማስታወሻው ይህ ሁኔታ “የሐፍረት እና ጥፋተኝት” ስሜት ውስጥ እንደጣለውም አብራርቷል፡፡
የሐሪሰን ማን ሀገር አሜሪካ፣ እስራኤል በጋዛ ንጹሐን ላይ ለምትፈጽመው መጠነ ሠፊ ጥቃት፣ የጦር መሣሪያ እና የስለላ ድጋፍ ትሰጣለች፡፡ ሀገሪቱ ለእስራኤል በምትሰጠው ድጋፍ ሳቢያ እንደ ጦር መኮንኑ ሁሉ፣ ሥራቸውን የለቀቁ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን የአሜሪካ ጋዜጦች ጽፈዋል፡፡
ጋዜጦቹ ከእነዚህ ውስጥ በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ውስጥ ከአስር ዓመት በላይ የሠራውን ጆሽ ፖል የተባለ ግለሰብ፣ በስቴት ዲፓርትመንት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ክፍል ውስጥ ባልደረባ የነበረችውን አኔል ሼኒል፣ በዚያው ስቴት ዲፓርትመንት ውስጥ የዐረቢኛ ቃል አቀባይ የነበረችውን ሐላ ራህሪትን ዘርዝረዋል፡፡
አሜሪካ የምትደግፋት እስራኤል ከመስከረም 2016 ጀምሮ በጋዛ በምትፈጽመው ጥቃት ቢያንስ 35 ሺሕ ንጹሐን ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 14 ሺሕ ሕፃናት ይገኙበታል፡፡












