Homeዜናና ወቅታዊዜናበደንቢያ ወረዳ በሚገኝ መስጅድ ኢማም ላይ ታጣቂዎች ግድያ መፈፀማቸውን የክልሉ መጅሊስ ገለጸ

በደንቢያ ወረዳ በሚገኝ መስጅድ ኢማም ላይ ታጣቂዎች ግድያ መፈፀማቸውን የክልሉ መጅሊስ ገለጸ

በአማራ ክልላዊ መንግሥት ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ውስጥ በሚገኘው ደንቢያ ወረዳ የሚገኝ መስጅድ ኢማም በታጣቂዎች ግድያ እንደተፈፀመባቸው የክልሉ መጅሊስ ኃላፊ ገለጹ። ግድያ የተፈፀመባቸው ኢማም ዕድሜ ከ75 ዓመት በላይ እንደሆነ ተነግሯል።

ትናንት ጁመዐ ግንቦት 9/2016 ግድያ የተፈፀመባቸው ኢማም ሸይኽ ሲራጅ ዐብድሬ የሚባሉ መሆናቸውን፣ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሸይኽ ዐብዱረሕማን ሡልጣን ለሚንበር ቲቪ ገልፀዋል። ዋና ጸሐፊው እንዳሉት፣ በአየንባ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ሸይኽ ሲራጅ ግድያ የተፈፀመባቸው አመሻሽ ላይ የመግሪብ ሰላት ሰግደው ሲወጡ ነው።

በሥም ያልተጠቀሱት ታጣቂዎች ኢማሙ ላይ ግድያ ከመፈፀማቸው በፊት እንግልት አድርሰውባቸዋል ተብሏል። ይህ እንግልት መሬት ለመሬት መጎተትን እንደሚያካትት ሸይኽ ዐብዱረሕማን አስረድተዋል።

ባለፉት ወራት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሙስሊም ነዋሪዎች የሚደርሱ ጥቃቶች መደጋገማቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የክልሉ ከፍተኛ ምክር ቤት ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

በክልሉ በቅርብ ጊዜ በሙስሊሞች ላይ ከደረሱ ጥቃቶች ውስጥ መጋቢት 29/2016 በባህር ዳር፣ ሞጣ እና ቢቸና ከተሞች የተፈፀመው ይጠቀሳል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሚያዝያ 1/2016 በሰጠው መግለጫ፣ በአማራ ክልል በሙስሊሞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ምክር ቤቱ ሲከታተል መቆየቱን በማስታወስ፣ “ሁኔታዎች ከዛሬ ነገ ይሻሻላሉ” በሚል “ነገሩን በትዕግሥት ለመያዝ ቢሞክርም” ሁኔታዎች ከመሻሻል ይልቅ “እየተባባሱ” መሄዳቸውን አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በክልሉ ጥቃት እየተፈጸባቸው ለሚገኙ ሙስሊሞች “በቂ ጥበቃና ከለላ” የመስጠት ኃላፊነት የአማራ ክልል መንግሥት እንደሆነም ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር። ሆኖም እስካሁን ድረስ በክልሉ ሙስሊሞች ተነጥለው ለሚደርሱ ጥቃቶች ከመንግሥት ፀጥታ አካላት በኩል የተሰጠ ማብራሪያ የለም።

በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ደንቢያ ወረዳ ትናንት በታጣቂዎች የተገደሉት ሸይኽ ሲራጅ ዐብድሬ፣ የሰባት ሴት እና ሦስት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ። [ሚንበር ቲቪ]

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular