የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ)፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚያካሄደው ምክክር ላይ የሕዝበ ሙስሊሙ አጀንዳ እንዲካተት፣ የተሳታፊ አካላት ልየታ በፍትሐዊነት በድጋሚ እንዲቃኝ ጠየቀ፡፡ ምክር ቤቱ ከኮሚሽኑ ተወካዮች ጋር ባካሄደው ውይይት በተሳታፊ እና አወያይ ደረጃ የሙስሊሞችን ተሳትፎ መረጃ ቢጠይቅም ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል፡፡
መጅሊስ የሕዝበ ሙስሊሙ አጀንዳ እንዲካተት የተሳታፊ አካላት ልየታ በፍትሐዊነት በድጋሚ እንዲቃኝ የጠየቀው፣ ሰኞ ግንቦት 5/2016 በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በደብዳቤው ሚያዝያ 25/2016 ከኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ ጋር በተወካዮቹ አማካይነት ውይይት መደረጉን አስታውሶ፣ ሆኖም ከአንድ ሳምንት በፊት ሚያዝያ 30/2016 በድጋሚ ውይይት ተደርጎ የሙስሊሞችን ተሳትፎ የሚያሳይ መረጃ እንዲሰጠው ጠይቆ የነበረ ቢሆንም እስካሁን እንዳልተሰጠው አስታውቋል፡፡
መጅሊስ ለፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በአስቸኳይ ውሳኔ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ሁለት ጉዳዮችንም አስፍሯል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ኮሚሽኑ ለምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን ልየታ ያጠናቀቀባቸውን 10 ክልሎችን እና የከተማ አስተዳደሮችን እንዲሁም ልየታ ያልተካሄደባቸውን አማራ እና ትግራይ ክልሎችን የሚመለከት ነው፡፡
ምክር ቤቱ የሚሳተፉ አካላት ልየታ ተከናውኖባቸዋል በተባሉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ስብጥሩ በድጋሚ እንዲታይ ሲጠይቅ፣ ለዚህ ምክንያት ነው ያለው “የሙስሊሞች ተሳትፎ በሕዝቡ ቁጥር ልክ” መሆን ስላለበት እንደሆነ አስገንዝቧል፡፡ በተመሳሳይ ልየታ ባልተካሄደባቸው አማራ እና ትግራይ ሙስሊሞች እኩል ተሳታፊነት እንዲኖራቸው እንዲደረግ ከወዲሁ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስቧል፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር ይችላል የተባለው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ውጪ እና ግጭት ባለባቸው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልልች አንዳንድ አካባቢዎችን ሳያካትት በ10 ክልሎችን እና የከተማ አስተዳደሮች ለምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን ልየታ ማካሄዱን ለመገናኛ ብዙኃን ገልጿል፡፡
ነገር ግን በተሳታፊ ልየታ ወቅት የተካተተው የሙስሊሙ ቁጥር ከ2 በመቶ እንደማይበልጥ መጅሊስ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በእስላማዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ከሚሠሩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች እና አንቂዎች ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ውይይት ለማካሄድ በሒደት ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በታኅሣሥ 2014 በጸደቀ የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች፣ በመንግሥት እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮችን እንደሚለይ አሥፍሯል።
ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡለትን እነዚህን አጀንዳዎች ካደራጀ በኋላ ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የመለየት ሚና በአዋጁ ተሰጥቶታል። ተወካይ ያስመርጣሉ ተብለው ከተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን እና የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የተገለሉ ኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ዕድሮች እና የንግዱ ማኅበረሰብ ተካተዋል። በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት አልተካተቱም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












