በሐላል ኢንዱስትሪ ላይ የሚያተኩረው 15ኛው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጉባዔ ትናንት ረቡዕ በሩስያ ተታርስታን ክልል ተጀመረ፡፡ የ‘ካዛን ፎረም’ በሚል ሥያሜ የሚታወቀው ጉባዔ፣ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ውስጥ ሐላል ኢኮኖሚ ተካቷል፡፡
የሩስያ ፌዴሬሽን እና የሙስሊሙ ዓለም ሀገራት የሚሳተፉበት ጉባኤ፣ ሐላል ምርቶች እና አገልግሎቶች በሥፋት ይቀርቡበታል የተባለውን የሩስያ ሐላል ኤክስፖ የሚያስተናገድ ነው፡፡ በዚህ ኤክስፖ የአፍሪካን ጨምሮ የመካከለኛው እና ምሥራቅ እስያ የፋይናንስ ተቋማት፣ ኩባንያዎች እንዲሁም የኪነ ሕንጻና ሌሎችም ባለሞያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑበት ይጠበቃል፡፡
ከሐላል ኢኮኖሚ ባሻገር በኢኮኖሚ ትብብር፣ በፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት፣ በሣይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ በቢዝነስ ትብብር፣ በሰው ኃይል ልማት፣ በባሕል እና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚያተኩረው ፎረም፣ ለአምስት ቀናት ቆይቶ የፊታችን ቅዳሜ ይጠናቀቃል፡፡
የካዛን ፎረም ባለፈው ዓመት ከ80 የዓለም ሀገራት 16 ሺህ ጎብኚዎች የተሳተፉበት ነው፡፡ ከእነዚህ ጎብኚዎች ውስጥ በርካታ ቁጥር የያዙት የዓለም አቀፍ እስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል ሀገራት ዜጎች ነበሩ፡፡
የፎረሙ አዘጋጆች በተያዘው ዓመት በተመሳሳይ ከ80 በላይ ሀገራት ዜጎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸውን የአናዶሉ ኤጀንሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፣ ባሕሬን፣ ማሌዥያ፣ ቱርክ፣ ኢራን እና ሊቢያ ከተሳታፊ ሀገራት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡












