የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባለፈው ሣምንት መገባደጃ ቀናት 2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄዷል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ጠቅላይ ምክር ቤቱን ጨምሮ የዘካና አውቃፍ ኮሚሽን፣ የወጣት ካውንስሎች በውጭ ኦዲተር እንዲመረመሩ የሚጠይቀው ሐሳብ መነሳቱን ጠቅላይ ምክር ቤቱ ባጋራው መረጃ አስታውቋል። ይህ የተነሳው የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን፣ ዕቅዶችንና የሥራ መመሪያዎችን ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርቦ ባስጸደቀበት ወቅት እንደሆነ ተገልጿል።
ይህን ዋቢ በማድረግ “ሚንበር ቲቪ” ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 30/2019 “ጠቅላይ ምክር ቤቱን ጨምሮ የዘካና አውቃፍ ኮሚሽን፣ የወጣት ካውንስሎች በውጭ ኦዲተር ምርመራ እንዲደረግባቸው ሐሳብ ቀረበ” በሚል አርእስት ለክቡራን ተከታታዮቹ በድረ ገጽ ዜና አጋርቷል።
ይሁን እንጂ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የአስተዳደር ድጋፍ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ዓብዱረዛቅ ነጋሽ፣ ጠቅላይ ምክር ቤቱን ጨምሮ የኢትዮጵያ መስሊሞች ልማት ኤጀንሴ (ኢሙልኤ)፣ አወሊያ፣ የዘካና አውቃፍ ኮሚሽን እንዲሁም የወጣቶች ካውንስል “በውጭ ኦዲተር ምርመራ እንዲካሄድ በማድረግ” ለጉባኤው ሪፖርት ማቅረቡን በመግለጽ መረጃው እርማት እንዲደረግበት ጠይቀዋል። በአሁኑ ሰዓት ሪፖርቶቹ በኦዲት እና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን በኩል እየተገመገሙ መሆኑንም የተናገሩት ኦፊሰሩ፣ ኮሚሽኑም “የራሱን የሒሳብ መዛግብት በውጭ ኦዲት ማስመርመሩን” ለጉባኤው አቅርቧል ብለዋል። (ሚንበር ቲቪ)












