የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በመዲናዋ ከሚገነባው የነጃሺ እስላማዊ ማእከል ግንባታ ዲዛይን ለውጥ ጋር በተገናኘ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ተነስቷል ላለው ጥያቄ በሰጠው ማብራሪያ፤ “ፕሮጀክቱን የሚያደናቅፉና የሥራ መንፈሥን የሚያዳክሙ” ያላቸው ዘመቻዎች “እንዲቆሙ” ሲል አሳስቧል። ከፍተኛ ምክር ቤቱ ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 30/2019 ባወጣው መግለጫ ነው፡፡
ከፍተኛ ምክር ቤቱ በመግለጫው፤ በነጃሺ እስላማዊ ማዕከል ግንባታ ዙሪያ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ሲሰራጩ የቆዩ “አስተያየቶችን”፣ “ሐሳቦችንና” “መረጃዎችን” ሲከታተል መቆየቱን ገልጿል፡፡ በዚህም ተሠራጭተዋል ያላቸውን መረጃዎች “እውነታውን ያላገናዘቡ” ሲል ያጣጣለው ከፍተኛ ምክር ቤቱ፤ አስተያየቶችና ዘመቻዎች “የበጎ አድራጊዎችን ሞራል ሊነኩ”፣ “የጠቅላይ ምክር ቤቱን ጥረት ሊያሳንሱና በማኅበረሰቡ ውስጥ ውዥንብር ሊፈጥሩ ይችላሉ” ሲል ፈርጇቸዋል፡፡ አክሎም “ለኡማው ጥቅም ሲሉ ንብረታቸውንና እውቀታቸውን የሚያበረክቱ ባለሀብቶችን ቅን ልቦና የሚያዳክሙ” ያላቸውን ዘመቻዎች “የፕሮጀክቱንም የደረጃ በደረጃ አፈጻጸም ያላገናዘቡና” ተገቢ አለመሆናቸውን አመልክቷል፡፡
በዚህ መነሻ ሕዝበ ሙስሊሙ ስለ ፕሮጀክቱ ትክክለኛ ሁኔታ እንዲያውቅ በሚል በሰጠው ማብራሪያ፤ የቀደመው ዲዛይን “በወቅቱ በተደረገው ግምት እስከ 13 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ” ይጠይቅ እንደነበር ጠቅሷል። በዚህም ግንባታውን በሀገር ውስጥ አቅም ለማስፈጸም እና በአጭር ጊዜ ለመገንባት “ሁኔታዎች ምቹ” እንዳልነበሩ በማስታወስ፤ ፕሮጄክቱ የወቅቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ክለሳ እንደተደረገበት አስታውቋል፡፡
ክለሳ ተደርጎበታል የተባለው አዲሱ ፕሮጀክት፤ በ5.5 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ እና በ8 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግንባታው ተጀምሯል ተብሏል፡፡ በአንድ ጊዜ “ከ45 ሺሕ በላይ” ምዕመናንን ማስተናገድ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
በመጀመሪያው ዲዛይን የተካተቱት የትምህርት፣ የባህልና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች አልተሰረዙም ያለው ምክር ቤቱ፤ የመስጂዱ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ በሚከናወነው ሁለተኛ ምዕራፍ በተቀናጀ መልኩ ይገነባሉ ብሏል፡፡
ይህ ፕሮጀክት ከወረቀት ወደ ተግባር እንዲሸጋገርና ግንባታው እንዲጀመር በተለይም በሸይኽ ሙሐመድ ሑሴን አል አሙዲ ባለቤትነት ሥር የሚንቀሳቀሰው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕና ከዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ጀማል አሕመድ ጎን ተሰልፈዋል ያላቸውን “ታላላቅ ባለሀብቶች” በሚል የወል ሥም ላጠቃለላቸው ግለሰቦች ምሥጋና አቅርቧል፡፡ ከፍተኛ ምክር ቤቱ ለገንቢዎቹ ምሥጋናውን ባቀረበበት መግለጫ፤ ክለሳ ተደርጎበታል ያለውን የማዕከል ግንባታ ይፋ ሳያደርግ ቀርቷል፡፡
የነጃሺ ማእከል ግንባታን በዋነኝነት መያዙ የተነገረለት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ተወካይ ዛሕራ ዓብዱልሐኪም ግንባታውን በአንድ ዓመት ተኩል አጠናቀው እንደሚያስረክቡ ጥቅምት 23/2019 በተከናወነው የግንባት ማስጀመርያ መርሐ ግብር ላይ ተናግረዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












