ኢትዮጵያ በሦስት ወራት ውስጥ ከቡና ወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) 878.52 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታውቋል። በመጪ ንግድ መዳረሻነት ሳዑዲ ዐረቢያ ቀዳሚ የኢትዮጵያ ቡና ተረካቢ ሆናለች፡፡
ባለሥልጣኑ የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት አፈጻጸምን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ ያስመዘገበው 878.52 ሚሊዮን ዶላር ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ15 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ብሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት ውስጥ 131 በላይ ቶን ቡና በመላክ የእቅዱን 91 በመቶ ማሳካት ተችሏል ተብሏል። የኢትዮጵያ ቡና ከተላከባቸው ሀገራት መካከል ሳዑዲ ዐረቢያ ቀዳሚውን ደረጃ ያገኘችው 22 በመቶው የሚሆነውን የኢትዮጵያ ቡና ኢምፖርት በማድረግ ነው፡፡
ጀርመን 17 በመቶ እንዲሁም ቻይና 12 በመቶው በመቀበል የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል የተጠቀሱ ሲሆን፣ አሜሪካ እና ቤልጂየም እንዲሁ ተካተዋል። ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ፣ ጣልያን እና ሩሲያ 10 ታላላቅ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ አገራት እንደሆኑ የቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ገልጿል።
ባለሥልጣኑ የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ከፍ በማድረግ በበርካታ የዓለም ገበያዎች ላይ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁሟል። በብራዚል ከፍተኛ የምርት አቅርቦት ሳቢያ የዓለም የአረቢካ ቡና ዋጋ ማሽቆልቆሉ ቢነገርም፣ የኢትዮጵያ ምርት አዎንታዊ አፈጻጸም ማሳየት መቻሉንም ባለሥልጣኑ ገልጿል። (ሚንበር ቲቪ)












