የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ያስገነባው፤ የኢትዮጵያ ሚዲያ የልሕቀት ማዕከል የምርቃት ሥነ ሥርዓት የተካሄደው በዛሬው እለት ነው፡፡
የጋዜጠኝነት እና የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አቅምን ለማጎልበት ያለመ መሆኑ የተለገጸው ማዕከሉ፤ የጋዜጠኞችን እና የመገናኛ ብዙኃን አመራሮችን እውቀት፣ ክሕሎት እና የሥነ ምግባር ደረጃ ማሻሻል ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ እንደሆነም ተዝርዝሯል፡፡
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ሬድዋን ሑሴን፣ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት የሀገርን ጸጥታ፣ የሕዝብን አንድነት እና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታን ሳይፈጥሩ በሀገራዊ ጥቅም እና በሕዝብ ደኅንነት ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው ሀገርን ማገልገል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን የነፃነት መኖር የተጠያቂነት አለመኖር ማለት እንዳልሆነ የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን ነፃነት እና ተጠያቂነት በዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ የማይነጣጠሉና ተመጋጋቢ መርሆዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
የመናገር ነፃነት ግለሰቦች ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ እና መረጃን እንዲያሰራጩ መብት የሚሰጥ ቢሆንም ማንኛውንም ነገር ያለገደብ ለመናገር ወይም ከሚመጣ ተጠያቂነት ነፃ ለመሆን የሚያስችል አይደለም።
ሃይማኖት ይሁን የብሄር ግጭትን ማነሳሳት፣ የግለሰቦችን ስም ሆነ ብሎ ማጥፋትና ክብርን ማጉደፍ ወይም ጥላቻን ማስፋፋት በነጻነት ሥም የሚፈጸም ስህተት መሆኑን በመግለጽ፤ ጋዜጠኞችና ሚዲያ ተቋማት መረጃን ከማስተላለፋቸው በፊት በጥንቃቄ መመዘንና ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አሳስበዋል። (ሚንበር ቲቪ)












