የኢንዶኔዥያ የፋይናንስ አገልግሎት ባለሥልጣን የእስላማዊ የንግድ ፋይናንስን ከወቅፍ ተኮር ማኅበራዊ ፋይናንስ ጋር የሚያገናኝ እንዲሁም የእስላማዊ ፋይናንስ ኢንዱስትሪን ልማት ለማስተባበር አዲስ እቅድ ይፋ አድርጋለች፡፡
እቅዶቹ በዚህ ሣምንት ይፋ የተደረጉበት የኢንዶኔዥያ እስላማዊ ፋይናንስ ጉባኤ ላይ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ርምጃውን የወሰደው የሀገሪቱን የእስላማዊ ፋይናንስ ሥነ ምህዳር ለማጠናከር እንደሆነ ገልጿል።
የኢንዶኔዥያ ፋይናንስ ዘርፍ እስከ መስከረም 2019 ድረስ አቅሙ 182.26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። ዓመታዊ የ9.28 በመቶ ዕድገት ያለው ይህ ዘርፍ፤ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የፋይናንስ ንብረት 11.21 በመቶውን የሚሸፍን ነው፡፡
በእስላማዊ ፋይናንስ መሪ እቅድ ከሚታቀፉ ዘርፎች መካከል ባንክ፣ ካፒታል ገበያ፣ ተካፉል፣ ዋስትና እና የጡረታ ፈንድ ተካተዋል። በተጨማሪም የፋይናንስ ተቋማት፣ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ፈጠራና ዲጂታል የፋይናንስ ንብረቶችም ተጠቅሰዋል።
ሀገሪቱ ይፋ ያደረገችው የእስላማዊ ፋይናንስ እቅድ ተወዳዳሪና ፈጠራ ያለው የፋይናንስ ኢንዱስትሪን ማልማት እንዲሁም አካታችና እርስ በርስ የተሳሰረ የፋይናንስ ሥነ ምሕዳር ማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል። በዘርፉ መካከል ደንቦችን፣ ፈቃድና ቁጥጥርን ማጣጣምም እንዲሁ ዋና ትኩረቱ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ኢኒሼቲቩ ከምርቶች በቀታይ ለሚፈጸም ሽያጭ የሸቀጡ ዋጋ አስቀድሞ የሚከፈልበት “ሰላም” እና ያለተመረተን እቃ ለማስመረት የሚደረገውን የሽያጭ ውል “ኢስቲስና”ን እንዲሁም በሸሪዓ መርሆች የሚመሩ የወርቅ ክምችት እንቅስቃሴዎችንም ያካተተ መሆኑ ተገልጿል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች በቴክኖሎጂና ሳይበር ደኅንነት፣ በሰው ኃይል ልማት እና በእስላማዊ ማኅበራዊ ፋይናንስ ይደገፋሉ ተብሏል።
የባለሥልጣኑ የባንክ ቁጥጥር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዲያን ኤዲያና ራኢ ኢኒሼቲቩ ዓላማ ያደረገው ቀደም ሲል በተናጠል የየራሳቸውን ፍኖተ ካርታ ሲያዘጋጁ የቆዩ የእስላማዊ ፋይናንስ ዘርፎችን ማገናኘት ነው ብለዋል። (ሚንበር ቲቪ)












