ስዊድን፣ የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ አያያዝን በሚመለከት ባሉ የደኅንነት ሥጋቶች ምክንያት በሥራ ኮምፒውተሮቻቸው ላይ የኦፕንኤአይ ‘ቻት ጂፒቲ’ እና የአንትሮፒክ ‘ክላውድ’ ስሪቶችን መረጃ ለማሰስ እንዳይጠቀሙ አግዷል። ከጥቅምት 16/2019 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው እገዳው ከደኅንነት ሥጋቶች ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተገልጿል።
ውሳኔው የተላለፈው በ2018 አጋማሽ ላይ በስዊድን የትራንስፖርት አስተዳደር ሠራተኞች ይጠቀሙባቸው የነበሩ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሣሪያዎች ላይ በተደረገ ግምገማ ሲሆን፤ የኤአይ መሣሪያዎች የመንግሥት ሥራዎችን ለማከናወን “ችግር ያለበት” አጠቃቀም መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ነው።
ይህን ተከትሎም የስዊድን ባለሥልጣናት መረጃውን እንዴት መጠበቅ እና ደኅንነቱን ማስጠበቅ እንደሚቻል የሚገልጽ ስምምነት ሳይደረግ ምስጢራዊ መረጃዎችን ወደ እነዚህ የኤአይ ሞዴሎች ማስገባት፣ መረጃዎቹ ወደ ሞዴሉ ተወስደው ለሥልጠና እንዲከማቹ ሊያደርግ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።
የሀገሪቱ የመንግሥት ቢሮዎች የዲጂታላይዜሽን ዳይሬክተር ሚካኤል ቬተርክራንትስ “በእንደዚህ ዓይነት ስምምነቶች ጥበቃ የማይደረግላቸው መድረኮችን መጠቀም ለስዊድን መረጃ ደኅንነት አሉታዊ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል ሲል ዮሮኒውስ ዘግቧል፡፡
በዚህም የአሜሪካው ኩባንያ ከስዊድን መንግሥት ጋር ባደረገው የደኅንነት ስምምነት ውስጥ የተካተተው እና የደኅንነት ማጣሪያን ያለፈው የማይክሮሶፍት ኮፓይሎት እንደ አማራጭ እንዲጠቀሙ እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህ ሁኔታም ውስጥ ቢሆን የመንግሥት ሠራተኞች ሥራዎቻቸውን ለማገዝ በጥብቅ የደኅንነት ቁጥጥር ሥር ሆነው ኤአይ እንዲጠቀሙ ተፈቅዶላቸዋል። የተወሰኑ ሠራተኞችም በስዊድን ባለሥልጣናት በተዘጋጁ ልዩ የኤአይ ረዳቶች መድረክ በኩል ብቻ ቻት ጂፒቲን እና ክላውድን እንዲጠቀሙ የሚፈቀድላቸው ይሆናል ተብሏል። (ሚንበር ቲቪ)












