Homeዜናና ወቅታዊዜናኢትዮጵያ በእስላማዊ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ “አስደናቂ ዕድገት” ካስመዘገቡ ታዳጊ ሀገራት መካከል ተካተተች

ኢትዮጵያ በእስላማዊ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ “አስደናቂ ዕድገት” ካስመዘገቡ ታዳጊ ሀገራት መካከል ተካተተች

ዓለም አቀፍ እስላማዊ ፋይናንስ እ.አ.አ በ2025 ከነበረበት 6.5 ትሪሊዮን ዶላር በ61.5 በመቶ በማደግ በ2030 ወደ 10.5 ትሪሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል በ“ኢስላሚክ ኮርፖሬሽን ፎር ዘ ፕራይቬት ሴክተር ኤንድ ለንደን ስቶክ ኤክስቼንጅ ግሩፕ” በጋራ የወጣው የ2026 እስላማዊ ፋይናንስ ልማት አዲስ ሪፖርት አመለክቷል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በእስላማዊ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ አስደናቂ ዕድገት ካስመዘገቡ ታዳጊ አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ተጠቅሷል።

ሪፖርቱ በባንክ ዘርፍ የታየውን ዕድገት በተመለከተ ባብራራበት ክፍል የባንክ አገልግሎት አጠቃላይ በባህረ ሰላጤው ሀገሮች፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ በቱርክ እና በፓኪስታን መሪነት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይጠቁማል። ይሁን እንጂ እንደ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ  እና ማልዲቭስ ያሉ ሀገሮች በኢስላማዊ የባንክ ሐብት በማፍራት ረገድ የሁለት አኃዝ ዕድገት አስመዝግበዋል ብሏል፡፡

ሪፖርቱ እስከ 2030 ድረስ በዘርፉ ያለው አማካኝ ዓመታዊ ዕድገት 9 በመቶ እንደሚሆን ይተነብያል። ማሌዥያ በእስላማዊ ፋይናንስ ልማት አመልካች 136 ነጥብ በማስመዝገብ አንደኛውን ደረጃ ስትይዝ፤ ሳዑዲ ዐረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ፣ ኢንዶኔዥያ እና ፓኪስታንም ቀዳሚዎቹ አምስት ሀገሮች ውስጥ ተካተዋል፡፡

ከእነዚህ ሀገራት ውጪ ቱርክ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ቤኒን፣ አዘርባጃን እና ኡዝቤኪስታንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ለውጥ ማምጣታቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ “ተካፉል” በ9 በመቶ በማደግ ወደ 146 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጿል።

የእስላማዊ ፋይናንስ ኢንዱስትሪ በአሁኑ ወቅት በ98 ሀገራት ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የባንክ ዘርፍ ብቻውን 71 በመቶ ወይም 4.6 ትሊዮን ዶላር ድርሻ ይይዛል። በመላው አፍሪካ ሀገራት የእስላማዊ ፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ለማስጀመር አዲስ ማዕቀፎችን እያስተዋወቁ እንደሚገኙም አስታውቋል።

የሱኩክ ገበያ በ2025 11 በመቶ በማደግ ከ1.1 ትሪሊዮን ዶላር ተሻግሯል፡፡ ገበያውን በቀዳሚነት እየመራች የምትገኘው ሳዑዲ ዐረቢያ ነች። የጂኦፖለቲካዊ ክስተቶች ለፋይናንስ ተቋማት አዳዲስ ፈተናዎች መፍጠራቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋትን በመጥቀስ እስላማዊ ፋይናንስ ገበያዎች ለውጭ ጫናዎች ያላቸውን ተጋላጭነት አካቷል።

ምንም እንኳ የባህረ ሰላጤው ሀገራት ውስጥ ያሉ እስላማዊ ባንኮች በጠንካራ ካፒታል እና ክምችት (ሊኩዲቲ) አስተዳደራቸው ጽናት ቢያሳዩም ሌሎች ሀገራት በአንጻሩ ከዋጋ ግሽበት ጫናዎች፣ ከምንዛሬ ተለዋዋጭነት እና ከጥብቅ የገንዘብ ድጋፍ ሁኔታዎች ጋር ለተያያዙ አደጋዎች ተጋላጭ እንደነበሩ ሪፖርቱ አመልክቷል።

በተጨማሪም ኢንዶኔዥያ በትምህርት፣ በምርምር እና በዕውቀት ልማት መሪ ሆና ብትቀጥልም በአንጻሩ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ ገበያዎች የአቅም ውስንነት መኖሩን ጠቁሟል። ለዚህም በትምህርት፣ በሞያ ሥልጠና፣ በምርምር እና በኢንዱስትሪ ትብብር ላይ ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅም ሪፖርቱ አመልክቷል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular