በትግራይ ክልል ጥቅምት 16/2019 የመማር ማስተማር ሒደት ይጀመራል ሲል የክልሉ ትምህርት ቢሮ ማስታወቁን ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
ይህ የተገለጸው የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር አስፈጻሚ ሥራ ኃላፊዎች በመቐለ ከተማ የሚገኘውን አፄ ዮሐንስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከጎበኙ በኋላ ነው፡፡ የጉብኝቱ ዓላማ በትምህርት ቤቱ ያለውን ሁኔታ ለመመልከትና መደበኛውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር የተደረጉ ዝግጅቶችን ለመገምገም ነው ተብሏል፡፡
አስፈጻሚ ሥራ ኃላፊዎቹ ከመምህራን እና ከትምህርት ቤት አስተዳደር አካላት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ተወያይተው አቅጣጫ አስቀምጠዋል ያለው ዘገባው፤ መምህራንና ወላጆች የትምህርት ሥራው በስኬት እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የትምህርት ሒደቱ እንደገና መጀመሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱና በጉዳት ምክንያት የተቋረጠው የትምህርት አገልግሎት እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል።
መምህራን ተማሪዎችን በተገቢው ሁኔታ ለመቀበልና የትምህርት ሥራውን ለማስቀጠል፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ገበታ በመመለስ የትምህርት ሥራውን መደገፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የትግራይ ትምህርት ቢሮ ሰኞ ጥቅምት 16/2019 መደበኛውን የመማር ማስተማር ሥራ ይጀምራሉ ያለው ሁሉም ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ቢሮው መምህራንና ተማሪዎች ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ በተመደቡባቸው ትምህርት ቤቶች በመገኘት ትምህርት ለመጀመር ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል። (ሚንበር ቲቪ)












