በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ተደራሽነት ያለው የእንግሊዙ ሁለገብ ባንክና የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ኤች.ኤስ.ቢ.ሲ (HSBC)፣ ከእስልምና ሕግ ጋር በተጣጣመው የኢንቨትመንት ፈንዱ አማካኝነት ውዝግብ በተነሳበት የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ፓላንቲር ውስጥ ያካሄደውን ኢንቨስትመንት እንደገና ለመገመገም ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው፣ ባንኩ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው “ኔስት” የተሰኘው በብሪታንያ መንግሥት የሚደገፈው የሥራ ቦታ የፔንሽን ፈንድ የእስልምና ፈንዱ በፓለንቲር ውስጥ መካተቱ አሳሳቢ መሆኑን ለግዙፉ ባንክ ሪፖርት ካደረገ በኋላ ነው፡፡
ጉዳዩ መጀመርያ የተጋለጠው ሀይፈን የተሰኘ እስላማዊ ጉዳዮች ላይ ሽፋን የሚሰጥ ድረ ገጽ የባንኩ “ኢስላሚክ ግሎባል ኢኩቲ ኢንዴክስ ፈንድ” እ.አ.አ በ2026 አጋማሽ የ38 ሚሊዮን ዶላር የፓላንቲር አክሲዮኖችን መግዛቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው፡፡
ይህን መረጃ በመያዝ ሚድል ኢስት ዐይ አደርግኩት ባለው ማጣራት፣ ፈንዱ በዚህ ዓመት የመጀመርያ አጋማሽ ላይ ከእስራኤል ጦር ጋር ግንኙነት ባለቸው ኩባንያዎች ውስጥ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ አክሲዮኖችን ገዝቷል፡፡ ይህ ቁጥር ቀደም ሲል ሬይቲዮን በመባል ይጠራ የነበረውንና በዓለም ሁለተኛው ትልቁ የጦር መሣሪያ አምራች የሆነውን አርቲ ኤክስ ኩባንያ የ35.7 ሚሊዮን ዶላር አክሲዮኖች ግዥንም ያካትታል፡፡ ይህም የብሪታንያ ሙስሊሞች ባለማወቅ ከግጭቱ ትርፍ እያገኙ ሊሆን እንደሚችልም ጠቅሷል።
በዚህ ጉዳይ ፖለቲከኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተዋል። የእንግሊዝ የፓርላማ አባል አፍዛል ኻን የሸሪዓ ሕግን ለማክበር የተቋቋመ የኢንቨስትመንት ፈንድ ከእስራኤል ሠራዊት ጋር ግንኙነት ካለው እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ በሚያደርግ ኩባንያ ጋር 38 ሚሊዮን ዶላር ማውጣቱ “ለኢስላሚክ ፋይናንስ መርሆች ፍጹም ንቀት እና ውርደት ነው” ሲሉ አውግዘዋል።
ፈንዱም ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ንፁሐን ፍልስጤማውያንን በመግደል ድጋፍ ባደረገ እና ከእስራኤል ሠራዊት ጋር ግንኙነት ባላቸው ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት በማድረጉ ሊያፍርበት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የፓላንቲር ዋና ስራ አስፈፃሚ አሌክስ ካርፕ ቀደም ሲል እስራኤል የኩባንያቸውን ቴክኖሎጂ ተጠቅማ የተገደሉ ፍልስጤማውያንን “አብዛኞቹ አሸባሪዎች ናቸው” ማለታቸውም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የአክሲዮን ድርሻው ተቃውሞ ከተነሳበት በኋላ ከ40 ሺሕ በላይ አባላት ያሉት የኔስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ከኤች.ኤስ.ቢ.ሲ ጋር ውይይት መጀመራቸውን ገለጸዋል። በዚህም ባንኩ “ከደንበኞች የሚነሱ ማንኛውንም ስጋቶች በቁም ነገር እንመለከተዋለን፤ እናም የባለሀብቶችን እሴቶች የሚያሟላ መሆኑን ለመገምገም ከገለልተኛ የኤክስፐርት አማካሪዎች ጋር በመተባበር ጉዳዩን በጥንቃቄ እንመረምረዋለን” ብሏል። (ሚንበር ቲቪ)












