በአሜሪካ በቦስተን በሚገኘው ማስ ጄኔራል ብሪጋም የጤና ተቋም ተመራማሪዎች የጤና ምርምር ጥናት እንደተመላከተው፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፊትን ፎቶግራፍ በማንሳት (ሰልፊ) የሰዎችን ዕድሜ እንዲሁም የካንሠር ሕመምተኞችን በሕይወት የመቆየት ርዝማኔ ግምት ማስቀመጥ ችሏል ተብሏል።
በታዋቂው የሕክምና መጽሔት ‘ዘ ላንሴት ዲጂታል ሄልዝ’ ላይ የታተመው ጥናቱ፤ ‘ኤፍ.ኤይ.ኤች.አር-ፌስ’ (FAHR-Face) የተሰኘው አዲስ የኤአይ ሞዴል ከ40 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የፊት ምስሎች ላይ ተመርኩዞ የሰዎችን አጠቃላይ የጤና ሁኔታ መመርመር ችሏል።
ቴክኖሎጂው ሁለት አይነት የትንበያ መንገዶችን በሚከተለው ቴክኖሎጂው፤ በቀዳሚነት የተቀመጠው በሕክምና ሥያሜው Foundation Artificial Intelligence for Health Recognition (FAHR-FaceAge) በመባል የሚጠራው ነው። ይህም የሰዎችን አካላዊ እና ባዮሎጂካል ዕድሜ መገመት የሚችል ነው።
ሁለተኛው በቀጥታ ከፊት ፎቶ ላይ በመነሳት የካንሠር ሕመምተኞችን የመትረፍ ወይም የሞት አደጋን የሚተነብየው FAHR-FaceSurvival የሚባለው ነው።
በFAHR-FaceSurvival ሞዴል ተመራማሪዎቹ እንዳረጋገጡት በሞዴሉ ከፍተኛ የሞት አደጋ እንዳለባቸው ከተጠቆሙት 122 የካንሰር ታካሚዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወይም 52.5 በመቶ ከትንበያው በኋላ በ90 ቀናት ውስጥ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
በአንጻራዊነት በFAHR-FaceSurvival ሞዴል መሰረት ዝቅተኛ ተጋላጭነት አለባቸው ከተባሉ 975 ታካሚዎች ውስጥ 2 በመቶ ብቻ በ90 ቀናት ውስጥ መሞታቸው ተገልጿል። በሌላ በኩል ከትክክለኛው ዕድሜያቸው (Chronological age) አንጻር ፊታቸው ቢያንስ በ5 ዓመት አስቀድሞ የሚያረጅባቸው ታካሚዎች ከሌሎቹ ቡድኖች ጋር ሲነፃፀር የሞት አደጋ 21 በመቶ ከፍ ያለ ሆኖ ተገኝቷል።
እንዲሁም ፊታቸው ቢያንስ ከ5 ዓመት በላይ ወጣት ሆኖ የሚታይባቸው ታካሚዎች ደግሞ 17 በመቶ ዝቅተኛ የሞት አደጋ አሳይተዋል። እንደ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት እና ሌሎች የአኗኗር ዘይቤዎች ከፊት ዕድሜ መግፋት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸውም በጥናቱ ተመላክቷል።
ተመራማሪዎቹ እንደገለጹት፣ የዚህ የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ሞዴል “አልጎሪዝም” የተለያዩ የፊት ክፍሎችን ማለትም የአፍንጫ ሸንተረር፣ ከዓይን በታች ያሉ አካባቢዎችን፣ ግንባርን እና የከንፈር ዙሪያ መስመሮችን በመተንተን ከጤና ሁኔታ ጋር የተያያዙ ንድፎችን ይለያል።
በማስ ጀነራል ብሪጋም የካንሰር ኢንስቲትዩት የጨረር ኦንኮሎጂስት እና የጥናቱ ጸሃፊ ዶክተር ሬይመንድ ማክ እንደተናገሩት የዚህ ቴክኖሎጂ ዋና ዓላማ ዶክተሮች የግል የካንሰር ሕክምና ውሳኔዎችን ሲያደርጉ ተጨማሪ መረጃ በመስጠት ለመደገፍ እንጂ፣ ዶክተሮችን ለመተካት ወይም በሽታን በራሱ ለመመርመር እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ሚንበር ቲቪ)












