Homeዜናና ወቅታዊዜናበስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የድምጽ መቅረጫ መሣሪያ የተከለው የኦፕን ኤአይ መሐንዲስ ከሥራ ተሠናብቶ...

በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የድምጽ መቅረጫ መሣሪያ የተከለው የኦፕን ኤአይ መሐንዲስ ከሥራ ተሠናብቶ ክስ ተመሠረተበት

ዋና መቀመጫውን ሳንፍራንሲስኮ ባደረገው የአሜሪካው የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ኩባንያ ኦፕን ኤአይ ውስጥ በመሐንዲስነት ይሠራ የነበረው የሳዑዲ ዐረቢያ ዜጋ፣ ኩባንያው የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የድምጽ መቅረጫ መሣሪያ ከተገኘ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ዓብዱረሕማን አልፈውዛን የተባለው የ35 ዓመት የሳዑዲ መሐንዲስ ከሐምሌ 2017 ጀምሮ በኩባንያው ውስጥ ሲሠራ እንደነበር ገልጿል፡፡ ዐቃቤ ሕግ አልፈውዛን የድምጽ መቅረጫ መሣሪያውን በመጠቀም “ምሥጢራዊ መረጃዎችን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ሰብስቧል” ሲል ክስ አቅርቦበታል፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው፤ ማክሰኞ እለት ለመጀመርያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበው የኦፕን ኤአይ መሐንዲስ፣ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት እና 250 ሺሕ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊጣልበት ይችላል፡፡

ይህ አጋጣሚ ኩባንያዎች እና ሀገራት የበላይነትን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት፣ በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ዘርፍ ውስጥ ስለሚደረጉ ስለላዎች አዲስ ሥጋት መደቀኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ “ጉዳዩን በጥብቅ እንደያዙት” የገለጹት የአሜሪካ ባለሥልጣናት፣ የሱፐር ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂን የተመለከቱ የአዕምሯዊ ንብረት ስርቆቶች በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ሥጋት ይፈጥራሉ እያሉ ይገኛሉ፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር ክስ እንደሚያስረዳው፣ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ተሸሽጎ የተገኘው መሣሪያ የተተከለው መስከረም 18 ሲሆን፣ ከሁለት ቀን በኋላ መስከረም 20 ተደርሶበታል፡፡ ዐቃቤ ሕግ እንዳብራራው፣ አልፈውዛን መሣሪያው ከመገኘቱ በፊት በነበሩ የተለያዩ ቀናት ከፍተኛ ምሥጢራዊ ስብሰባ በሚያስተናግደው በሥራ አስፈጻሚዎች የስብሰባ አዳራሽ አቅራቢያ መታየቱን በኦፕን ኤአይ ቢሮዎች የደኅንነት ካሜራ ምስል ተረጋግጧል፡፡

የኦፕን ኤአይ የደኅንነት ሠራተኞች ሁለተኛ የድምጽ መቅረጫ መሣሪያ በአልፈውዛን ቦርሳ ውስጥ ማግኘታቸው ተዘግቧል፡፡ ኦፕን ኤአይ በማኅበራዊ ሚዲያ ባወጣው መግለጫ፤ “ተጠርጣሪው የድምጽ መቅረጫ ቢተክልም፣ የኩባንያውን ውድ የቴክኖሎጂ ምስጢሮችንና የመረጃ ቋት ስለመውሰዱ ማረጋገጫ የለንም” ብሏል፡፡

የዘርፉ ባለሞያዎች እንደሚሉት በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ዓለም ውስጥ ዋናው እና “ውድ አዕምሮ” የሚባለው የሒሳብ ቀመር ውጤት ነው፡፡ ይህ አንድ የኤአይ ሞዴል ሲሰለጥን ያገኘውን እውቀትና ችሎታ የሚያስቀምጥበት ምሥጢራዊ ቁልፍ በመሆኑ፣ ይህ ከተሰረቀ ሌላ አካል ሙሉውን ቴክኖሎጂ በቀላሉ አባዝቶ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ሠራተኛው ይህን መውሰድ ባይችልም ኩባንያው ከሥራ እንዳሰናበተው ገልጿል፡፡ ኩባንያው አክሎም መሣሪያውን ተክሏል የተባለውን ግለሰብ ለመለየት የራሱን አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ሞዴሎች እንደተጠቀመም ጠቁሟል፡፡

የኦፕን ኤአይ መሐንዲስ የነበረው አልፈውዛን የኤሌክትሪክ፣ ሜካኒካል ወይም ሌሎች መሣሪዎችን በመጠቀም የሰዎችን የቃል ንግግር ለመጥለፍ በመሞከር ወንጀል ተከሷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular