ባለፈው ወር የእስላማዊ ባንክ ሕግ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው ኡዝቤኪስታን፤ በሸሪዓ መርሕ የሚሠሩ ባንኮችን፣ የማይክሮ ፋይናንስን ተቋማትን፣ የብድር ዋስትና ኤጀንሲንና ሌሎችንም ተቋማት ለማስተባበር የእስላማዊ ፋይናንስ ምክር ቤት ይፋ አድርጋለች፡፡
ምክር ቤቱ፤ ብሔራዊ መስፈርት የማውጣት፣ መተዳደሪያ ደንብ የመቅረጽ፣ የቁጥጥር እና ክትትል ምክረ ሐሳቦች ዝግጅት፣ ለፋይናንስ ተቋማት እገዛ የማድረግ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ደረጃ አውጪ ተቋማት ጋር በሚደረግ ግንኙነት ማዕከላዊ ባንኩን ወክሎ የመሥራት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
አምስት አባላትን ያቀፈው ምክር ቤቱ፣ አራቱን የተመረጡለት ከሀገሪቱ ፈትዋ ማዕከል ነው፤ አንደኛው አባል ደግሞ ከባንክ ዘርፍ የተወከሉ የዘርፉ ኤክስፐርት ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ በዚህ መልኩ የተዋቀረው የሸሪዓ ዕውቀትን ከፋይናንስ ጋር አጣጥሞ ለመምራት በማሰብ መሆኑን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡ ይህ ምክር ቤት በዓመቱ መጨረሻ ሪፖርት የሚያቀርበው ለሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነው፡፡
ኡዝቤኪስታን በእስላማዊ ፋይናንስ ማዕቀፍ ላይ ለበርካታ ዐመታት ስትሠራ መቆየቷ ይነገራል፡፡ እ.አ.አ በ202 የወጣው የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በእስላማዊ መርሆች ላይ የተመሠረቱ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ፈቅዷል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ የወጡ ዝርዝር መመርያዎች ደግሞ ካፒታል እና ሥራ የሚያጣምረውን “ሙዳረባህ”፣ ሙሉ አጋርነትን በሚሰጠው “ሙሻረካ”፣ የኪራይ ውል በሚሰጠው “ኢጃራ” እና የቅድመ ክፍያ ንግድ ውሉን “ሰላም” የተሰኙትን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮችን አካተዋል፡፡
የሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ በእስላማዊ ፋይናንስ አገልግሎቶች ቦርድ እገዛ ከ2026 እስከ 2030 የሚሆን ብሔራዊ የእስላማዊ ፋይናንስ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ፍኖተ ካርታ ባንክን፣ የካፒታል ገበያዎችን፣ የኢንሹራንስ ዘርፍን፣ የሞያ ሥልጠናን እና ሰፊውን ማዕቀፍ ያጠቃልላል፡፡
እስላማዊ ፋይናንስ ወለድን የሚከለክል ሲሆን፣ በአጠቃላይ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ከሐብት (ንብረት)፣ ከንግድ፣ ከኪራይ (ሊዚንግ)፣ ወይም ከሥጋት መጋራት ጋር የተያያዙ እንዲሆኑ ይጠይቃል፡፡
የዓለም አቀፉ የእስላማዊ ፋይናንስ ሐብት መጠን 5.98 ትሪሊዮን መድረሱን ይፋዊ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ እንደ አይሲዲ-ኤላኢሳኢጂ እና ኤስ ኤንድ ፒ ግሎባል ሬቲንግስ የደረጃ ምዘና እና ምርምር ተቋማት ሪፖርቶችም፤ የእስላማዊ ባንክ፣ ሱኩክ (ቦንድ) እና ተካፉል (ኢንሹራንስ) ዘርፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡












