የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሱዳን ባካሄደው ምርመራ፤ በሰሜን ዳርፉር ግዛት ዋና መቀመጫ አል ፋሽር ከተማ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በጥቅምት በተፈጸመው ጥቃት የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡ ሪፖርቱ በከተማው ለሦስት ቀናት የነበረውን ሁኔታ “እጅግ አስፈሪ” እንደነበር ይገልጻል፡፡
የድርጅቱ ተልዕኮ ሊቀመንበር ሙሐመድ ቻንዴ ዑስማን፤ በፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ጀነራል ሙሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው ቡድን የፈጸመው ጥቃት “በስፋቱ፣ በቅንጅቱ እና የነበረው ሕዝባዊ መሠረት” የተፈፀሙት ወንጀሎች በጦርነት ውስጥ “በዘፈቀደ ኃይል በመጠቀም ብቻ” የተፈጠሩ አለመሆናቸውን አመልካች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ለዚህ ሪፖርቱ በአል ፋሽር እና በአካባቢው 320 የዓይን እማኖችን እና ተጎጂዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡ የቡድኑ አባላት ወደ ቻድ እና ደቡብ ሱዳን የምርመራ ጉብኝቶችን አካሂደዋል። በወቅቱ በተፈጸመው የዘፈቀደ ግድያ ጎዳናዎች በደም ተሞልተው ይታዩ እንደነበርም አሥፍሯል፡፡ በተጨማሪም ሪፖርቱ ዐረብ ያልሆኑ ማኅበረሰቦች በተለይም “ዛጋዋ” የተባሉ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የወሲብ ጥቃት የተፈፀመባቸው “ኤል-ፋሽር ሥልጣን ከያዙ በኋላ” መሆኑን ያመለክታል። ጥቃቱ የተፈጸመባቸው “ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ ከሰባት እስከ 70 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶችና ልጃገረዶች ናቸው”፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀደም ሲል ባወጣው መረጃ፤ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አል ፋሽርን ከተቆጣጠረ በኋላ በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ስድስት ሺሕ ሰዎች መገደላቸውን ሲገልጽ፤ የብሪታንያ የፓርላማ አባላት ደግሞ በአጠቃላይ ከ60 ሺሕ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርት አድርገዋል፡፡ የከተማዋ 150 ሺሕ ገደማ ነዋሪዎችም የደረሱበት አልታወቀም።
በታኅሣሥ ወር ዬል ሂዩማኒቴሪያን ሪሰርች ላብ ያሠራጨው ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በአል ፋሽር የተፈጸሙ የጅምላ ጭካኔዎችን ለመሸፋፈን ዘመቻ አካሄዷል፡፡ ማስረጃዎችን ለማዳፈን ከተደረጉ ሙከራዎች መካከል አስከሬኖችን ማቃጠል ይገኝበታል፡፡ ተጎጂዎች እና የረድኤት ሠራተኞች እንደሚሉት፤ ቡድኑ ከከተማዋ ለመሸሽ የሞከሩ ዜጎችን በማፈን ደማቸውን ያለፍቃዳቸው ሲቀዳ ነበር፡፡ የላቦራቶሪው ትንታኔው አክሎም በሳተላይት የተነሱ 38 ምስሎች ደም ወይም ሌሎች የሰውነት ፈሳሾችን ያሳያሉ፡፡ የሪሰርች ማዕከሉ ይህ የሚያመለክተው የፈሰሰው ደም ከጠፈር ሊታይ እንደሚችል ነው ብሏል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












