Homeዜናና ወቅታዊዜናየዱባዩ ዲፒ ወርልድ በሳዑዲ ዐረቢያ ጂዳ ኢስላሚክ ወደብ ላይ ያለውን ድርሻ በከፊል...

የዱባዩ ዲፒ ወርልድ በሳዑዲ ዐረቢያ ጂዳ ኢስላሚክ ወደብ ላይ ያለውን ድርሻ በከፊል ሸጠ

በጭነት ሎጂስቲክስ፣ በወደብ ተርሚናል ሥራዎች፣ የባህር ላይ አገልግሎቶች እና የነፃ ንግድ ዞኖች ላይ የሚንቀሳቀሰው የዱባዩ ዲፒ ወርልድ፤ በሳዑዲ ዐረቢያ በጂዳ ኢስላሚክ ወደብ ተርሚናል ውስጥ ያለውን ድርሻ በከፊል የሸጠው ለዴንማርኩ የሎጂስቲክስ ኩባንያ ኤፒ ሞለር ሚርስክ ነው፡፡

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ፤ ሁለቱ ኩባንያዎች በጅዳ ኢስላሚክ ወደብ በደቡባዊ ኮንቴይነር ተርሚናል “ስትራቴጂካዊ አጋርነት” ለመመሥረት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቋል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ሜርስክ በተርሚናሉ ውስጥ የ37 ነጥብ 5 በመቶ አናሳ ድርሻ ሲያገኝ፤ ዲፒ ወርልድ ደግሞ የ62 ነጥብ 5 በመቶውን የአብላጫ ድርሻ ይይዛል፡፡

ዲፒ ወርልድ በሳዑዲ ዐረቢያ ውስጥ ከፊል ድርሻውን ለሜርስክ የመሸጡ ዜና የተሰማው ሳዑዲ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ቀይ ባሕርን ጨምሮ በየመን እና ሱዳን ልዩነታቸው በሰፋበት ወቅት ነው፡፡ ሁለት ሀገሮች በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ከፍተኛ የሚባል “ዲጂታል ውጊያ” ላይ ተሰማርተዋል፡፡

የሳዑዲ ዐረቢያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አቡ ዳቢ ከእስራኤል ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነት ያወግዛሉ። የሁለቱን ሀገሮች ውዝግብ በተመለከተ ሚድል ኢስት ዐይ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ፤ ዐረብ ኤምሬትስ ሳዑዲ ዐረቢያን በፀረ ሴማዊነት እንዲኮንኑ በእስራኤል ደጋፊ የአሜሪካ ሎቢ ቡድኖች ላይ ጫና ማሳደራቸውን አጋልጧል፡፡

ዘገባው የጂዳ እስላማዊ ወደብ ደቡባዊ ኮንቴይነር ተርሚናል የኤምሬትስ ባለቤትነት የሁለቱ ሀገሮች ምንም እንኳን ልዩነታቸው ቢሰፋም በኢኮኖሚ እርስ በእርስ የተሳሰሩ መሆናቸውን ያረጋግጣል ብሏል። ዲፒ ወርልድ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ ውስጥ ለዐረብ ኤምሬትስ ኃይሏን እና ተፅእኖን ለማሳየት ቁልፍ ሚና ሲጫወት መቆየቱ ይነገራል፡፡

ዲፒ ወርልድ እስራኤል በቅርቡ የሀገርነት እውቅና በሰጠቻት ሶማሊላንድ የበርበራ ወደብ ባለቤት ነው፡፡ ወደቡ ከኢትዮጵያም ጋር ሥሙ የሚነሳ ነው፡፡ በተባበሩት ዐረብ ኤሚሬትስ የኢፌዲሪ ልዩ መልእክተኛ እና ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር እና የዲፒ ወርልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሡልጣን አሕመድ በኢትዮጵያና በኩባንያው መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት ባለፈው ዐመት ኅዳር ወር አድርገው ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular