- ማኅበሩ ባለፈው ዓመት መገባደጃ ዓለም አቀፍ የገቢ ማሳባሰቢያ ዘመቻውን ያካሄደው በ“ሚንበር ቲቪ” ነው
በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርንያ ግዛት በቤይ ኤሪያ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚ የሆነው ‘የቤይ ኤሪያ ሙስሊም ኢትዮጵያን ማኅበር’ (Ethiopian Bay Area Muslims Association – EBAMA)፤ በእሳት ቃጠሎ የወደመበትን ማዕከል ለመተካት አዲስ ሕንጻ ግዢ መፈጸሙን አስታውቋል፡፡
ማኅበሩ ባሠራጨው መግለጫ እንዳሳወቀው፤ የሕንጻ ግዢውን የፈጸመው በ2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የግዢው ሒደት ከሸሪዐ ጋር በማይጻረር መልኩ ክፍያውን ሙሉ በሙሉ ተፈጽሟል፡፡ ካሉት 204 አባላት መካከል ከ37ቱ ከወለድ ነፃ በሦስት ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ 600 ሺሕ ዶላር ብድር ማሰባሰብ መቻሉንም ገልጿል፡፡
‘የቤይ ኤሪያ ሙስሊም ኢትዮጵያን ማኅበር’ የገዛው ሕንጻ የመሰብሰቢያ ማዕከል እና መስጅድን በስሩ ያካተተ ነው፡፡ በሳንሆዜ 14ኛ መንገድ ላይ የሚገኘው ማዕከሉ፤ ከሳንሆዜ ዩንቨርሲቲ የቅርብ ርቀት ላይ በመገኘቱ “ለሙስሊም ተማሪዎችና የአካባቢው ሙስሊም ነዋሪዎች” ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሕንፃውን ሙሉ በሙሉ ተረክቦ ፍቃድ በማውጣት የእድሳት ሥራዎችን አከናውኖ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝም የማኅበሩ መረጃ ይጠቁማል፡፡
እ.አ.አ ከ2001 አንስቶ ከ20 ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የዕውቀት እና የተርቢያ ማዕከል በመሆን ያገለገለው ማዕከሉ፤ “በድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ” ውድመት የደረሰበት በነሐሴ 2016 (ሴፕቴምበር 5/2024) ነበር፡፡ ከዚህ ክስተት በኋላ በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ያለ ማዕከል ቀርቷል፡፡
ማኅበሩ የወደመውን ንብረት ለመተካት የድጋፍ ማሰባሰብ በኦንላይን ገንዘብ መሰብሰቢያ አማራጭ እንዲሁም ሜይ 5/2025 የተካሄደውን ዓለም አቀፍ የድጋፍ ማሰብሰብ ፕሮግራሙን ደግሞ በሚንበር ቲቪ ዩትዩብ ቻናል በማዘጋጀት በርካቶች ተሳተፈዋል፡፡

የቤይ ኤሪያ ሙስሊም ኢትዮጵያን ማኅበር (EBAMA)፣ በቤይ ኤሪያ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ለማገልገል የተመሠረተ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። (ሚንበር ቲቪ)












