የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኻሊድ ሚሽዓል የሚመሩት የፍልስጤም ቡድን፤ በጋዛ ላይ የውጭ አገዛዝ ለመጫን የሚደረገውን ማንኛውንም ሙከራ እንደሚቃወም በኳታር ዋና ከተማ ዶሐ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ ተናግረዋል፡፡ ሐማስ ከእስራኤልና ከአሜሪካ የጦር መሣሪያ እንዲፈታ ጥሪ ቢቀርበለትም ተግባራዊ እንደማያደርግም ገልጸዋል፡፡
በንግግራቸው የቡድናችንን “መከላከያ፣ የጦር መሣሪያዎቹን እና መሪዎቹንን ወንጀለኛ ማድረግን መቀበል የለብንም” ብለዋል። “ወረራ እስካለ ድረስ ተቃውሞ ይኖራል፤ ተቃውሞ በወረራ ስር ያሉ ሰዎች መብት ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
በጋዛ በጥቅምት ወር በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡት የተኩስ አቁም ስምምነት ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ ላይ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ተሻግሯል፡፡ በዚህ ምዕራፍ የሐማስ ትጥቅ መፍታት እና የእስራኤል ጦር ቀስ በቀስ በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች እንደሚወጣ ሠፍሯል፡፡
እ.አ.አ ከ2007 ጀምሮ ጋዛን የሚያስተዳድረው ሐማስ የጦር መሣሪያዎቹን ሊያስረክብ የሚችለው በፍልስጤም ለሚመራው አስተዳስተዳር መሆኑን ከዚህ ቀደም አስታውቋል፡፡ የቀጣናው አስተዳደር በፕሬዝዳንት ትራምፕ በሚመራው “የሰላም ቦርድ” ሥልጣን ስር ለጊዜው በተቋቋመ 15 ፍልስጤማውያን ቴክኖክራቶች ለሚመሩት ኮሚቴ ይተላለፋል።
የሐማስ መሪ በኮንፍረንሱ ላይ ያነሱት ሌላው አጀንዳ የጋዛ መልሶ ማልማት እና የረድኤት አቅርቦት ጉዳይ ነው፡፡ “የሰላም ቦርዱ” ጋዛን መልሶ ለመገንባት እና ሰብአዊ ርዳታ እንዲገባ የሚያስችል “የተመጣጠነ አካሄድ” መከተል እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡ “ፍልስጤማውያን በፍልስጤማውያን ሊተዳደሩ ይገባል። ጋዛ የሕዝቧ እና የፍልስጤም ንብረት ናት። የውጭ አገር የበላይነትን አንቀበልም” ብለዋል፡፡
ሚድል ኢስት ዐይ የእራኤሉን ሐአሬትዝ ጋዜጣ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የእስራኤል ባለስልጣናት ከጋዛ መልሶ ግንባታ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት የሚያስችሉ መንገዶችን እየፈለጉ ነው። የፋይናንስ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ከእስራኤል ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጋር ሊኖሩ ስለሚችሉት ዕድሎች መወያየታቸውን የዘገበው ጋዜጣው፤ ከግንባታዎቹ መካከል ጋዛን ከእስራኤል ጋር የሚያገናኝ አውራ ጎዳና ግንባታን ያጠቃልላል። የእስራኤል ባለሥልጣናት በጋዛ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ላይም የኢኮኖሚ ዕድሎች ካሉ በሚል ተወያይተዋል። (ሚንበር ቲቪ)












