በአዳዲስ መልቲ ሚዲያ ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀው “የኢትዮጵያ ሙስሊም አዋርድ”፤ በዛሬው እለት ተከናውኗል። በዚህ የክብር እና የልሕቀት ፕሮግራም በቅዱስ ቁርኣን የአማርኛ ትርጉም እንዲሁም በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምሥረታ ጉልሕ ሚና የተጫወቱት ሸይኽ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ በመባል ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ዕውቅናውን ተወካያቸው በመድረኩ ተቀብሏል።
ዛሬ ቅዳሜ ጥር 30/2018 በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወነው የሽልማት ፕሮግራም፤ በሌሎች ዘርፎችም አሸናፊዎች ተለይተዋል።
በዚህም በሚንበር ቲቪ ሐሙስ ምሽት የሚቀርበው “ኸሚስ ምሽት” በምርጥ ፕሮግራም ዘርፍ እንዲሁም “የኔ መንገድ” አዘጋጅ ሶፊያ ጁሐር በምርጥ ሴት ጋዜጠኛ ማሸነፍ ችለዋል። በምርጥ ፕሮግራም ዘርፍ የተመረጠው “ኸሚስ ምሽት” 256ኛ መሰናዶውን በዚህ ሣምንት አቅርቧል።

የዛውያ ቲቪው ዲኑ ዓሊ በወንድ ጋዜጠኛ ዘርፍ ሲመረጥ፣ በዲጂታል አማራጮች መስኮት ትዩብ በዩትዩብ እና ሙጂብ አሚኖ በፌስቡክ ተመርጠዋል። በፌስቡክ በሴቶች የተመረጠችው አቲካ አሕመድ ዓሊ ነች።
በሐላል ቱሪዝም በዑምራ መሰናዶ ዙበይር ትራቭል፤ ሙስሊም ውሜንስ ግሩፕ በሀገር ውስጥ የጉዞ አገልግሎት ተሸላሚ ሆነዋል። በሥነ ጽሑፍና በኪነ ጥበብ ደራሲ ፉአድ ሙና “ኢፋዳ” በተሠኘ ድርሰት፣ አሕመድ ነጋ በምርጥ ፎቶግራፈር፣ በአጭር ፊልም ሦስት ተወዳዳሪዎች እና በነሺዳ ኑር አምባ ተመራጭ ሆኗል። ሐምዛ ሺፋ በዳዕዋና በኢስላማዊ ትምህርት ዘርፍ በቲክቶክ ሲመረጥ፣ አሚር በመረጃ እና ጠበቃ ዐዲስ ሙሐመድ በቲክቶክ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴት በመባል ተመርጣለች።
የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች እንደገለጹት፤ የአሸናፊዎች ምርጫ የተካሄደው ለምርጫ በተዘጋጀ ድረ ገጽ አማካኝነት የሕዝብ ድምጽ ከተሰበሰበ በኋላ በሕዝብና በባለሞያዎች ተለይተው ነው።
የኢትዮጵያ ሙስሊም አዋርድ ቀድሞ ዕጩዎችን ባስተዋወቀበት ጊዜ በእጩዎች ዝርዝር ላይ ጥያቄ ሲነሳበት ነበር። በዚህም አንዳንድ እጩዎች ራሳቸውን አግልለዋል። (ሚንበር ቲቪ)












