የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የአየር ትራንስፖርት አቅርቦት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ዛሬ ሐሙስ ጥር 7/2018 በአዲስ አበባ ከተማ ስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጀው ሥነ ሥርዐት ላይ፤ ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ሐጅና ዑምራ ዘርፍ ተጠሪ ሸይኽ ሙሐመድ ሷሊህ እና የአየር መንገዱ የአዲስ አበባ ሽያጭ ክፍል ዳይሬክተር አቶ አማን ወሌ ናቸው፡፡ በዚሁ ወቅት በዘንድሮ ዐመት ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ የመጀመርያውን በረራ የሚያደርጉበት ሚያዝያ 10/2018 እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
አየር መንገዱ እስከ ሰኔ 23/2018 ድረስ ሑጃጅን ከአዲስ አበባ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያዋ ጂዳ ከተማ በደርሶ መልስ የማጓጓዝ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ለሐጅ ከሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ምእመናን አብላጫውን ቁጥር የሚያመላልሰው አየር መንገዱ፤ በዘንድሮ ዐመት የሚያጓጉዛቸው የምእመናን ቁጥር 3 ሺሕ መሆኑን በተፈራረሙት ሰነድ ላይ ሠፍሯል፡፡ “ተመዝጋቢ ምዕመናንን ያማከለ በረራዎችን ለመመደብ” ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አየር መንገዱ አስታውቋል። ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ የሳዑዲ ዐረቢያውን “ሳዑዲያ” አየር መንገድ ለሑጃጅ አገልግሎት ሲጠቀም ነበር፡፡
ባለፈው ዐመት ከኢትዮጵያ በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ የተሳተፉ ምእመናን ቁጥር 6 ሺሕ 500 እንደነበር የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡ በተያዘው ዐመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመመዝገብ በእቅድ የተያዘውን አኅዝ በተመለከተ እስካሁን ይፋ አላደረገም፡፡ በአንጻሩ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ታኅሣሥ 7/2018 በሰጠው መግለጫው፤ ከሁሉም ክፍለ ከተማዎች 2 ሺሕ 500 ሑጃጅ ለመመዝገብ እቅድ እንዳስቀመጠ ገልጾ ነበር፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከዚህ አስቀድሞ ከኢምግሬሽን አገልግሎት ጋር በተገናኘ ለሐጅ ሥነ ሥርዓት ተሣታፊ ምዕመናን ቅድሚያ የሚስተናገዱበት አሠራር እንዲኖር ለማስቻል ስምምነት መፈራረሙንም የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ተጠሪው በዛሬው ሥነ ሥርዐት ላይ አስታውሰዋል። ጥር 18/2018 እንደሚጠናቀቅ የተገለጸው የዘንድሮ የሐጅ ምዝገባ የሚከናወነው አዲስ አበባ፣ ጅግጅጋ እና ሞያሌን ጨምሮ በ30 ከተሞች ነው፡፡
የዘንድሮው ዐመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት የሚከናወነው ከግንቦት አጋማሽ አንስቶ ነው፡፡ ዋንኛ የሐጅ ተግባራት የሚከናወኑት ከግንቦት 17 እስከ ግንቦት 22/2018 ባሉት ቀናት ውስጥ ይሆናል፡፡ በዚህም ግንቦት 17 “የውመል ተርዊያህ” በመባል የሚጠራው ቀን ይሆናል፡፡ በማግሥቱ ግንቦት 18 የ“አረፋ” እለት እንዲሁም ግንቦት 19/2018 “ዒድ አል አድሓ” እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የሥነ ሥርዐቱ የመጨረሻዎቹ ቀናት በቀጣይ ወራት ጨረቃ መታየት ላይ ይመሠረታሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












