Homeዜናና ወቅታዊዜናሙስሊም ወንድማማችነት የአሜሪካን ፍረጃ ለመቃወም “ሁሉንም ሕጋዊ መንገዶች” እንደሚከተል አስታወቀ

ሙስሊም ወንድማማችነት የአሜሪካን ፍረጃ ለመቃወም “ሁሉንም ሕጋዊ መንገዶች” እንደሚከተል አስታወቀ

አሜሪካ በግብፅ፣ በሊባኖስ እና በዮርዳኖስ የሚገኙ በዐረቢኛ ሥያሜው “ኢኽዋነል ሙስሊሚን” (ሙስሊም ወንድማማችነት) በመባል የሚጠራውን ድርጅት በ“አሸባሪነት” መፈረጇን አስታውቃለች፡፡ ውሳኔው የተሰማው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደራቸው ድርጅቶቹን በጥቁር መዝገብ ውስጥ ለማስገባት ሂደት እንዲጀምር መመርያ ከሰጠ ከሣምንታት በኋላ ነው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የግምጃ ቤት መምርያ፤ በዮርዳኖስና በግብጽ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን “በተለይ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች” ብሎ ሲፈርጅ፤ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ደግሞ የሊባኖሱን ድርጅት “የባዕዳን አሸባሪ ድርጅት” በሚል ምድብ አስቀምጦታል፡፡ ይህ ምድብ በጥቁር መዝገቡ ዝርዝር ውስጥ “የከፋ ደረጃ” የሚባለው ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት የሚነገረው ድርጅቱ፤ አሸባሪ ተብሎ በመፈረጁ በድርጅቱና በአባላቱ ላይ የጉዞና የኢኮኖሚ ማእቀቦች የሚጣሉ ይሆናል፡፡

ውሳኔውን ያሳለፉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ሙስሊም ወንድማማችነትን በአሸባሪነት ለመፈረጅ እቅድ እንደያዙ ሲናገሩ የነበረው በቀደመው የሥልጣን ዘመን እ.አ.አ በግንቦት 2019 ነበር፡፡ በወቅቱ የግብፁ ፕሬዝዳንት ዐብዱልፈታህ አል ሲሲ በአሜሪካ ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ በዚሁ ወቅት ዶናልድ ትራምፕ ይህን እንዲያደርጉ አል ሲሲ ጥያቄ ማቅረባቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ትራምፕና አል ሲሲ መገናኘታቸውን ተከትሎ ትራምፕ ወዲያውኑ ቡድኑ ላይ የኢኮኖሚ ማእቀብ መጣል የሚቻልበትን መንገድ እንዲፈልጉ ለደኅንነትና የዲፕሎማሲ አማካሪዎች ትእዛዝ አስተላልፈው ነበር። ነገር ግን ተግባራዊ ሳይደረግ የመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው ተጠናቋል፡፡

ለትራምፕ “ቡድኑን በሽብር ፈርጀው” ያሉት የቀድሞው ወታደር አል ሲሲ፤ በ2013 ፕሬዝዳንት የነበሩትን የሙስሊም ወንድማማችነት መሪ ሙሐመድ ሙርሲን በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ማውረዳቸው የሚታወስ ነው። ሙርሲ ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ አባላትም ታስረዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት የአል ሲሲ ጥያቄ ከቀረበ ከስድስት ዐመታት በኋላ ትናንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ የሙስሊም ወንድማማችነት አካላት “ሕጋዊ የሲቪክ ድርጅት እንደሆኑ ቢገልፁም ከጀርባ ግን እንደ ሐማስ ያሉ የሽብር ቡድኖችን በግልፅ እና በጋለ ስሜት ይደግፋሉ” ሲል ውንጀላ አቅርቧል፡፡

ይሁን እንጂ የግብፅ ተወካይ ሳላህ ዐብዱልሐቅ ውንጀላውን ውድቅ አድርገውታል፡፡ “በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙስሊሞችን ይጎዳል” ያሉትን ይህን ውሳኔ ቡድናቸው ለመቃወም “ሁሉንም ሕጋዊ መንገዶች ይከተላል” ብለዋል። እንደ ተወካዩ ከሆነ፤ የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔውን እንዲያሳልፍ ያደረገው “ከእስራኤል እና ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ የሚመጣው ጫና” ነው፡፡

“የግብጹ ሙስሊም ወንድማማችነት ሽብርተኝነትን መርቷል፣ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፣ ቁሳዊ ድጋፍ ያደርጋል አልያም በሽብርተኝነት ተሰማርቷል የሚሉ ክሶችን በሙሉ እንቃወማለን” ሲሉ ለአልጀዚራ ተናግረዋል።

በአንጻሩ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሀገሪቱ ሙስሊም ወንድማማችነት ቅርንጫፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ “አሸባሪ” ተብሎ መፈረጁን “አስፈላጊ ርምጃ ነው” በማለት በደስታ እንደተቀበለው አስታውቋል፡፡

በ1928 በግብጻዊው ሐሰን አል በና የተመሠረተው የሙስሊም ወንድማማችነት፤ በመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ማኅበራዊ ድርጅቶችን ጨምሮ ቅርንጫፎች አሉት። ቡድኑ እና ተባባሪዎቹ “ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጠኛ” መሆናቸውን ይናገራሉ። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular