የሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት በዘንድሮው የ1447 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ እድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ሊኖር በሚችለው ከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ ሊከተል ከሚችለው ንዳድ ለመጠበቅ፤ እንዳይሳተፉ የከለከሉት አዲስ ባወጡት መመርያ ነው። መመርያው የወጣው በአጠቃላይ ምእመናን ላይ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ እንደሆነ ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል፡፡
ለከልከላው መነሻ የሆነው በቅርብ ዓመታት በተከናወኑ የሐጅ ሥነ ሥርዓቶች በነበረው ከፍተኛ ሙቀት መጠን ሳቢያ በተከተለው ንዳድ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ነው። በዚህም ኑሱክ በተባለው የኦንላይን የሐጅ ምዝገባ መድረክ ላይ ለማመልከት አንድ ሰው እድሜው ቢያንስ 12 ዓመት መሙላት እንደሚኖርበት በቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል።
ባለፉት ሁለት ተከታታይ የሐጅ ወቅቶች የነበረው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ለሑጃጅ በተለይም ለሕፃናትና አዛውንቶች ትልቅ ፈተና የጋረጠ እንደነበር ባለሥልጣናት ይገልጻሉ። በ1445 ዓ.ሂ ከዓለም ዙርያ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ምእመናን ለሐጅ ሥነ ሥርዓት ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ተጉዘው ነበር፡፡ በወቅቱ በሙቀት ሳቢያ ከ1 ሺሕ 300 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
ሀገሪቱ በተመሳሳይ በባለፈው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ሕፃናት እንዳይሳተፉ ክልከላ ጥላ ነበር። በርካታ የእግር ጉዞ የሚጠይቀው የሐጅ ሥነ ሥርዐት በተከናወነባቸው የበጋው ወራት፤ በሳዑዲ የሙቀት መጠኑ በአማካይ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግረድ አልፏል፡፡
በአንጻሩ ባለፈው ዓመት በተከናወነው የሐጅ ሥነ ሥርዐት በንዳድ ምክንያት የሰው ሕይወት ማለፉ ሪፖርት አለመደረጉን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












