ዓለም አቀፉ የስኳር ሕመም ፌደሬሽን፤ በመላው ዓለም ከ20 እስከ 79 ዕድሜ ክልል ካሉት ውስጥ 589 ሚሊዮን ሰዎች ማለትም ከዘጠኝ ሰዎች አንዱ፤ ከስኳር ሕመም ጋር እንደሚኖር ያመለከተው አዲስ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል 252 ሚሊዮን ሰዎች ምርመራ አለማካሄዳቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ሳያውቁት በበሽታው ለከፍተኛ ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡
ፌዴሬሽኑ እ.አ.አ በ2024 ባወጣው ሪፖርት በስኳር በሽታ ሳቢያ በዘጠኝ ሴኮንድ ውስጥ አንድ ሰው ይሞታል፡፡ ለስኳር በሽታ መድኃኒት የሚውለው ወጪ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተሻግሯል። ይህ ለበርካታ ታዳጊ ሀገሮች ከባድ ፈተና የደቀነ ነው ተብሏል።
የስኳር በሽታ ከፍተኛ ምጣኔ ከተመዘገበባቸው ሀገሮች መካከል ቻይና በ148 ሚሊዮን ኬዞች ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛለች፡፡ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ኢንዶኔዥያ፣ አሜሪካ፣ ሳዑዲ ዐረቢያና ግብጽ ከ20 ሀገሮች ተርታ ተመድበዋል። የበሽታው ሥርጭት በከፍተኛ መጠን ከሚስፋፋባቸው 20 ሀገሮች ውስጥ ፓኪስታን ከፊት ረድፍ ስትሰለፍ፤ ኩዌት እና ሞሪሼስ ይከተላሉ።
የዓለም አቀፉ የስኳር ሕመም ፌደሬሽን ሪፖርት ታዳጊ ሀገሮች ቅደመ ምርመራ እና መከላከል እንዲሁም ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ትኩረት በማድረግ ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስቧል። በሪፖርቱ ትንበያ መሠረት፤ በ2050 የስኳር ሕሙማን ቁጥር ወደ 853 ሚሊዮን ከፍ ይላል፡፡ 81 በመቶ ገደማ ዝቅተኛ ወይም መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ይመዘገባል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












