የፍልስጤሙ ሐማስ በግብጽ ዋና ከተማ እየተካሄደ ከእስራኤል ጋር በሚገኘው የጋዛ ተኩስ አቁም፤ ለበርካታ ዓመታት በእስራኤል ወሕኒ የሚገኙትን የፈትሕ ከፍተኛ አመራሩ መለቀቅ ማካተቱ ተሰምቷል፡፡ የፍልስጤሙ ፈትሕ ከፍተኛ አመራር በመሆን የሚታወቁት የ65 ዓመቱ መርዋን፤ የቡድኑ መሥራች የያሲር አረፋት የቅርብ ሰው እንደነበሩ ይነገራል።
መርዋን ከዚህ ቀደም በተደረሰውና በእስራኤል ባለሥልጣናት በተጣሰው የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት በተመሳሳይ እንዲለቀቁ በሐማስ አቅራቢነት በኳታር አሚር ተሚም ቢን ሐማድ አስሣኒ እና የግብጽ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ሐሰን ማሕሙድ በኩል ግፊት ቢደረግም ሳይሳካ የቀረ ነው።
ሐማስ ከመርዋን ባርጉውሲ በተጨማሪ የቡድኑ መሪዎች ሐሰን ሰላም እና አባስ አስስይድ እንዲሁም የ ‘ዘ ፖፑላር ፍሮንት ፎር ዘ ሊበሬሽን ኦፍ ፓለስታይን’ መሪው አሕመድ ሳዳትም እንዲለቀቁ መጠየቁ ተነግሯል፡፡ ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው ከሆነ፤ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግለሰቦቹን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
ቡድኑ በካይሮ በፊት አውራሪነት የተወከለው በዋና ተደራዳሪው ኸሊል አል ሐያ አማካይነት ነው፡፡ አል ሐያ ለግብጹ የመንግሥት ቴሌቪዥን አል ቃሂራ በሰጡት እምብዛም ያልተለመደ ነው በተባለ ቃለ ምልልስ፤ ሐማስ ድርድሩን እያካሄደ ወደሚገኝበት ሻርም ኤል-ሸይኽ የመጣው “የሕዝባችንን ጭንቀት፣ ስቃይ፣ የከፈለውን መስዋእትነት በጫንቃችን ተሸክመን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በዚህም ዋና ዓላማው “ጦርነቱን ለማቆም፣ እስራኤል ከጋዛ ቀጠና ሙሉ በሙሉ እንድትወጣ፣ በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያን እስረኞች እንዲፈቱና ሕያዋንም ሆነ ሙት የእስራኤል ምርኮኞች እንዲለቀቁ” መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም “የሕዝባችንን የመረጋጋት፣ የነፃነት፣ የሀገር መመሥረት፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ግቦችን እና ሕልም ጭምር ይዘን እንሄዳለን” ብለዋል።

አል ሐያ ከዚሁ ጋር አያይዘው የዋስትናና ጉዳይ በማንሳት የጋዛን ተኩስ አቁም ሰነድ ያቀረበችው አሜሪካ መተማመኛ እንድተሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ መተማመኛውን ከአሜሪካ የጠየቁት “ወራሪው አካል ላይ አመኔታ ስለማናሳድር ነው”፤ ምክንያቱም “ደጋግሞ የገባውን ቃል ኪዳን በማፍረስ የሚታወቅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የትራምፕ አስተዳደር ባቀረበው እቅድ ላይ ለመስማማት “በጋዛ ላይ የሚካሄደው ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያበቃል” የሚል “እውነተኛ ዋስትና” እንዲሰጠን እንፈልጋለን ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአዎንታዊ መልኩ መቀጠሉ የተነገረለትን ድርድር ለመቀላቀል፤ በትራምፕ አስተዳደር ኅላፊነታቸው አይታወቅም የሚባሉት የፕሬዝዳንቱ አማች ጃሬድ ኩሽነር እና የትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ ቢሊዮነሩ ወዳጃቸው ስቲቭ ዊትኮፍ ወደ ካይሮ እንደሚጓዙ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ እንደ ዘገባዎች ከሆነ፤ ትራምፕ ኩሽነርን የላኩት በጉዳዩ ላይ አጽናኦት ለመስጠት ነው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ የኳታር፣ የግብጽ እና የቱርክ የስለላ ኅላፊ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












