Homeዜናና ወቅታዊዜናከኦክቶበር 7/2023 ወዲህ በፍልስጤም የሆነው…

ከኦክቶበር 7/2023 ወዲህ በፍልስጤም የሆነው…

እ.አ.አ የዛሬው እለት ኦክቶበር 7 ነው። ፍልስጤማውያን ከ2023 ወዲህ ለሁለት ዓመት ድፍን ዓመታት የእስራኤል ቦምብ እየዘነበባቸው ቆይተዋል፡፡ ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእስራኤል ጦር በሰነዘረው ጥቃት ቢያንስ 67 ሺሕ 160 ፍልስጤማውያንን ሲገደሉ፤ 169 ሺሕ 679 በጋዛ ውስጥ ቆስለዋል፡፡

ይህ አሐዝ በጦርነቱ ከተገደሉት 33 ሰዎች መካከል አንዱ ማለትም ከጦርነቱ በፊት ከነበረው የሕዝብ ብዛት 3 በመቶ ገደማ እንደማለት ነው። ከሟቾቹ መካከል ቢያንስ 20 ሺሕ የሚደርሱት ሕፃናት ሲሆኑ፤ ባለፉት 24 ወራት በየሰዓቱ አንድ ሕፃን ይገደላል።

የፍልስጤም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሟቾችን ቁጥር ሲመዘግብ የሚጠቀመው፤ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱትን ወይም በይፋ የተመዘገቡትን ሰዎች ብቻ በመሆኑ የሟቾቹ ትክክለኛ ቁጥር አይታወቅም፡፡ ምናልባትም አሁን ከተመዘገበው የበለጠ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ምክንያቱም በፍርስራሾች ውስጥ የሞቱት ወይም የጠፉ ሰዎች ቁጥር አልተካተተም።

በጋዛ ጥቃት ከተገደሉት በተጨማሪ ከ169 ሺሕ በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ያስተናገዱት  ጉዳት ሕይወታቸውን የሚቀይር ነው፡፡ ዩኒሴፍ በጋዛ ከ3 ሺሕ እስከ 4 ሺሕ የሚደርሱ ሕፃናት አንድ ወይም ከዚያ በላይ የአካል ክፍሎችን እንዳጡ ግምቱን አስቀምጧል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ቢያንስ 125 የጤና ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 34ቱ ሆስፒታሎች ናቸው፤ በዚህም ምክንያት ህሙማን መሥረታዊ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም።በእስራኤል በሆስፒታሎች ላይ በሚሰነዘረው ጥቃት እንዲሁም በአጠቃላይ በጋዛን በቀጠለው የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 1 ሺሕ 722 የጤና እና የርዳታ ሠራተኞች ተገድለዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ከሆስፒታሎችና ከሕመምተኞች አልጋዎች ታፍሰው በእስራኤል እስር ቤቶችና ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ታጉረዋል፡፡ 

እስከ ሐምሌ ወር ድረስ የእስራኤል ኃይሎች 28 ሐኪሞችን አግተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 18ቱ የቀዶ ጥገና፣ የማደንዘዣ ሐኪም፣ በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚሠሩ እና የሕፃናት ሐኪሞች ናቸው፡፡ ይህም የጋዛን የጤና ሥርዓት ወሳኝ የሚባሉ ባለሞያዎች ነጥቋል፡፡ ከነዚህ ከፍተኛ ሐኪሞች መካከል ሁለቱ በእስራኤል ማጎሪያዎች በደረሰባቸው እንግልት ሕይወታቸው ቢያልፍም አስከሬናቸው አሁንም ድረስ አልተገኘም፡፡ ድርጊቱ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሮማ ሕግ አንቀጽ 8 የደነገገውን በመጣሱ ማጥቃት የጦር ወንጀል ነው።

እስራኤል በጣለችው ወታደራዊ ገደብ አማካኝነት በጋዛ ውስጥ ረሃብ እንዲበረታ ሠርታለች፡፡ ለወራትእርዳታዎችን በማገድ እና ሰዎች ምግብ ለማግኘት በተሰበሰቡበት በየቀኑ ቦምብ ስታዘንብ ቆያታለች፡፡ በረሃብ ምክንያት 154 ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 459 ሰዎች ሞተዋል። ይህን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት የተደገፈው የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ ሥርዓት (አይፒሲ)፣ ዓለም አቀፍ የረሃብ መቆጣጠሪያ በጋዛ ውስጥ ረሃብ እንደተከሰተ በነሐሴ ወር ታውጇል፡፡

በልጆች ላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ጨምሯል:: በሐምሌ ወር ብቻ ከ12 ሺሕ በላይ ሕፃናት በከፍተኛ ሁኔታ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለባቸው ተረጋግጧል፤ ይህም በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከነበረው ስድስት እጥፍ ይበልጣል። ከኦክቶበር 2023 አንስቶ እስራኤል ቀድሞውኑ የተጎዱትን የጋዛን መሠረተ ልማቶች በተከታታይ ዒላማ አድርጋለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ እንደገለጸው፤ በነሐሴ ወር 92 በመቶ የሚሆኑት የመኖሪያ ቤቶችና 88 በመቶ የሚሆኑት የንግድ ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሰፈሮች ሙሉ ለሙሉ ተደምስሰው፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን መኖሪያቸውን አጥተው ተፈናቅለዋል። ድርጊቱ በተባበሩት መንግሥታት መርማሪ ቡድን እና በሰብአዊ መብት ቡድኖች ድርጊቱ በዘር ማጥፋት ተፈርጇል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይገታ የድርጊቱ ፊት አውራሪ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተፈጻሚ አልተደረገም፡፡

የእስራኤል ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ ዘገባ እየተሰናዳ በነበረበት ሰአት እንኳን የእስራኤል ጦር በኻን ዩኒስ በሰነዘረ የቦምብ ጥቃት ሕጻን ልጅ ተገድሏል፡፡ እስራኤል ባለፉት ሁለት ዓመታት በፈጸመችው ድርጊት ከበርካታ የዓለም ሀገሮች ውግዘት እያስተናገደች ቀጥላለች፡፡ ከቀናት በፊት በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኔታንያሁ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ሲራመዱ በርካታ ዲፕሎማቶች ስብሰባውን ረግጠው ሲወጡ ታይተዋል፡፡ በሌላ በኩል ለፍልስጤም ሀገርነት እውቅና የሚሰጡ ሀገሮችም ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡

ከዓለም ሀገሮች መካከል ባርባዶስ፣ አየርላንድ፣ ጃማይካ፣ ኖርዌይ እና ስፔንን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ እና የካሪቢያን አገራት ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት እውቅና የሰጡት በ2024 የፀደይ ወራት ነበር። ካናዳ እና ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያና እና ፖርቱጋል ደግሞ እውቅናውን የሰጡት ከቀናት በፊት ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

(የዚህ ጥንቅር ዋንኝው ምንጭ አልጀዚራ ሲሆን፣ የዩኤስ ቱዴይ መረጃም ተካቷል)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular