በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ ጁመዓ መስከረም 23/2018 ምሽት ላይ፤ የታጠቁ አካላት በከተማው በሚገኘው ኑር መስጅድ ጥሰው በመግባት ለረዥም ዓመታት በኢማምነት ያገለገሉትን ሸይኽ ጀማል ከማልን ጨምሮ አራት ሰዎች መግደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሚንበር ቲቪ ተናግረዋል።
በነዋሪዎች መረጃ መሠረት፣ ግድያው የተፈፀመው በመስጅዱ የዒሻ ሰላት ተጠናቆ ምዕመናን ከተበተኑ በኋላ ነው። ለሚንበር ቲቪ የተናገረ የዓይን እማኝ፣ ሰላት ሰግደው ከተበተኑ “በግምት ከ40 ደቂቃ በኋላ” የአዛን ድምጽ ከመስጅድ በድጋሚ መስማቱን በመግለጽ፣ ድምፁን ሲያወጡ የነበሩት ኢማሙ እንደነበሩ ተናግሯል። ይሁን እንጂ የአዛን ጥሪው ሳይጠናቀቅ ተኩስ መሰማቱን አስረድቷል።
በተኩሱ ከመስጅዱ ኢማምና የቦረና ወረዳ እስልምና ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ሸይኽ ጀማል ከማል በተጨማሪ፣ የወጣቶች ሰብሳቢው ቃሲም ዳኜ፣ የመስጅዱ ኻዲም ዓብዱልሰመድ ሙሐመድ እና በጥበቃነት የሚያገለግለው ኢማም ሙሐመድ ተገድለዋል።
ከተገደሉት በተጨማሪ የኑር መስጅድ ሙዐዚን ዓሊ ሐሰን በታጣቂዎቹ ታግተው መወሰዳቸውንም የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል። የሙዓዚኑ ሁኔታ እስካሁን ድረስ አልታወቀም። የአካባቢው ነዋሪዎች በአሁኑ ሰዓት የተገደሉ ምዕመናንን ቀብር ሥነ ሥርዐት ለመፈፀም አስከሬን የመከፈንና ጉድጓድ እያስተካከሉ ቢገኙም በከተማው ውጥረት መስፈኑን ተናግረዋል።
የቦረና ወረዳ የእስልምና ጉዳዮች ኀላፊዎች የተፈፀመውን ግድያ አረጋግጠዋል። ሚንበር ቲቪ በስልክ ያገኛቸው ፕሬዝዳንቱ ሐጂ ነስሩ ዓብዱልከሪም፤ ኢማሙን ጨምሮ ሌሎችም መገደላቸውን አረጋግጠዋል።
በጉዳዩ ላይ የአካባቢው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ የፀጥታ አካላት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የሰጡት መረጃ የለም። (ሚንበር ቲቪ)












