የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሥያሜውን “የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ” በሚል ለውጥ ማድረጉን ይፋ ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ንጉሥ ታደሰ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 22/2018 በሰጡት መግለጫ፤ ተቋሙ “የሕግ ጉዳዮችን ካጠናቀቀ በኋላ” በቅርቡ በአዲሱ ሥያሜ ብቻ እንደሚወከል አስረድተዋል፡፡
ከአሠራር ጋር በተገናኘም ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት የመንግሥት ሠራተኞችን ብቻ ተቀብሎ ሲያስተምር እንደነበር ያስታወሱት ንጉሥ ታደሰ (ዶ/ር)፤ በአዲሱ አሠራር የትምህርት ሚኒስቴርን መስፈርት የሚያሟሉ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን እንዲሁም ከግልና ከመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃንን ተቀብሎ ያስተምራል ብለዋል፡፡
ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር የመጣው፤ የትምህርት ሚኒስቴር መስከረም 12/2018 ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከ2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎችን ስለሚቀበል “ተማሪዎች ምርጫቸው ውስጥ ማካተት እንደሚችሉ” ከገለጸ በኋላ ነው፡፡
አሁን የሥያሜው ለውጥ ያደረገው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፤ የሀገሪቱን የሲቪል ሠርቪስ አቅም ለማጎልበት በሚል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ ሪፎርም ለማድረግ ጥናት እያካሄደ የሚገኝ ተቋም ነው። ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያሣየው፣ እያካሄደ የሚገኘው ሪፎርም የጥናት ውጤት ዩኒቨርሲቲው የወደፊት አቅጣጫ ምን መምሰል እንዳለበትና የሚመራበትም የህግ ማዕቀፍ የሚያሳይ ዝርዝር ጉዳዮችን ባካተተ መልኩ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ነው። በጥናቱ ውጤት እንደተመላከተውም የዩኒቨርሲቲው Public Service and Governance University በሚል ሥያሜ ቀደም ሲል እንደነበረው ለትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ በመሆን ይቀጥላል።
በዛሬው መግለጫም፤ ተቋሙ በአመራርና አስተዳደር ሀገሪቱ የምትመራበትን ሪፎርም በማመላከት፣ በፋይናንስ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በዲጃታላይዜሽንና ፈጠራ መስኮች ላይ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን ሒደት መጀመሩንም አረጋግጠዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በማኅበራዊ ሣይንስ እና ዲቨሎፕመንት ስተዲስ፣ ፐብሊክ ሴክተር ቢዚንስ እና ምጣኔ ሀብት እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን እና በፐብሊክ ሰርቪስ ኢኖቬሽን በትኩረት እንደሚሠራም ተጠቁሟል። (ሚንበር ቲቪ)












