Homeዜናና ወቅታዊዜናሦስት ዐረብ እና ሙስሊም ሀገሮች ሐማስ የፕሬዝዳንት ትራምፕን የጋዛ የሰላም ዕቅድ እንዲቀበል...

ሦስት ዐረብ እና ሙስሊም ሀገሮች ሐማስ የፕሬዝዳንት ትራምፕን የጋዛ የሰላም ዕቅድ እንዲቀበል ግፊት እያደረጉ ነው – አክሲዮስ

ኳታር፣ ግብፅ እና ቱርክ፤ የፍልስጤሙ ሐማስ በጋዛ የሚሰነዘረውን ጦርነት ለማስቆም በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለቀረበው እቅድ “አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ” ግፊት እያደረጉ እንደሚገኙ አክስዮስ የተሰኘው የአሜሪካ ዜና ምንጭ ዘግቧል።

ከሐማስ ጋር በጣም የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሀገሮቹ፤ በቡድኑ፣ በእስራኤል እና በአሜሪካ መካከል የመልዕክት ልውውጦችን በማድረስ እየሠሩ የሚገኙ ናቸው፡፡ በዘገባው መሠረት፤ የእነዚህ ሀገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከሐማስ መሪዎች ጋር ለሁለት ጊዜ ተገናኝተዋል። ይህ ውይይት የመጣው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ሐማስ ምላሹን እንዲያሳውቅ “ሦስት እና አራት ቀናት” እንደሚሰጡ ከተናገሩ በኋላ ነው፡፡

ትራምፕ በቨርጂኒያ ኩዋንቲኮ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጄኔራሎች እና የባሕር ኅይል መኮንኖች ባደረጉት ንግግር፤ “[የሐማስ መሪዎች] ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ይፈርማሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል። የአሜሪካ እና የእስራኤል ባለሥልጣናት መጠነኛ ጥርጣሬ ቢኖራቸውም፤ ሐማስ ለትራምፕ እቅድ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣል የሚል ግምት እንዳላቸውም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

ሰኞ ምሽት ትራምፕ እቅዱን ለዓለም ይፋ ሲያደርጉ፤ የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ቢን ዐብዱራህማን አስሳኒ እና የግብፁ የስለላ ኅላፊ ሐሰን ረሻድ በዶሃ ለሐማስ መሪዎች በተመሳሳይ እቅዱን እያቀረቡ እንደነበርም ተነግሯል፡፡ በወቅቱ በነበረው ውይይት ሁለቱም ባለሥልጣናት ሐማስ እቅዱን እንዲቀበለው አሳስበዋል። በተለይ አስሳኒ ለሐማስ መሪዎች የቀረበውን ስምምነት አሞካሽተውታል፡፡ አያይዘውም ከትራምፕ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ጦርነቱን ለማስቆም “ቁርጠኛ መሆናቸውንም አፅንዖት ሰጥተው ነግረውኛል” ብለዋል። ይህን ለሐማስ “በቂ ዋስትና ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ የሐማስ መሪዎች ለአስሳኒ በሰጡት ምላሽ እቅዱን መመርመር እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የስለላ ኅላፊው ማክሰኞ ዕለት በድጋሚ ከሐማስ መሪዎች ጋር በዶሐ ተገናኝተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የቱርክ የስለላ ዳይሬክተርሩ ኢብራሂም ካሊን አስከትለው ነበር፡፡

በትራምፕ የጋዛ እቅድ መሠረት፤ በቀጣይ ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር ግንኙነት የሌለው “ቴክኖክራቲክ” የፍልስጤም አስተዳደር ከጦርነቱ ማብቂያ በኋላ የገዛን አስተዳደር ይረከባል። ነገር ግን ይህ የፍልስጤም አመራር የሚመረጠው በመሬቱ ባለቤት በፍልስጤም ሕዝብ ሳይሆን፤ የሰላም እቅዱን ተግባራዊነት በሚቆጣጠር አዲስ ዓለም አቀፍ አካል ነው። ትራምፕ “የሰላም ቦርድ” ሲሉ የጠሩት ይህ አካል፤ ስምምነቱ እንዲሳካ የማድረግና ቁልፍ የቀጣናው እንዲሁም ዓለም አቀፍ መሪዎችን የማሰባሰብ ኃላፊነት እንደሚሰጠው ተናግረዋል። የቁጥጥር አካሉ ሊቀመንበር ራሳቸው እንደሚሆኑም ተናግረዋል።

ትራምፕ ራሳቸው በሚመሩት ቦርድ ሌሎች መሪዎችም እንደሚካተቱ ጠቁመዋል፡፡ በቦርዱ ውስጥ መካተት ይፈልጋሉ ከተባሉ ግለሰቦች መካከል አንደኛው የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ይገኙበታል። ነገር ግን ሐማስ እና ሌሎች ቡድኖች በቦርዱ ውስጥ “ምንም ዐይነት ሚና እንደማይኖራቸው” ተገልጿል፡፡ ትራምፕ ባቀረቡት እቅድ ላይ ድርድር እንደማይኖርም ገልጸው ነበር፡፡

አክሲዮስ ግን የአሜሪካ ባለሥልጣናት በሙሉ እቅዱ ክፍሎች ላይ ባይሆንም፤ ሐማስ ማብራሪያ በሚጠይቅባቸው ወይም በማሻሻያነት በሚያቀርባቸው ጉዳዮች ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular