Homeዜናና ወቅታዊዜናአዲሱ የትራምፕ የገዛ እቅድ፤ ከተማዋን ከመጠቅለል - “እንደራሴ” ወደ መሾም?

አዲሱ የትራምፕ የገዛ እቅድ፤ ከተማዋን ከመጠቅለል – “እንደራሴ” ወደ መሾም?

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ እለት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ፤ “በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማስፈን ተቃርበናል” ሲሉ ተደመጡ፡፡ “የምናገረው ስለ ጋዛ ብቻ አይደለም፤ ጋዛ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ የምናወራው ከጋዛ ባሻገር ስላለ ብዙ ነገር ነው። ሁሉም ነገር መፍትሔ እያገኘ ነው” አሉ፡፡

ከዚህ ንግግር በኋላ በጋዛ ላይ የሚሠነዘረውን የእስራኤልን ጦርነት ለማስቆምና በፍልስጤም ግዛት የሚገኙ የእስራኤል ምርኮኞችን ለማስለቀቅ አዲስ ባለ 20 ነጥብ እቅድ ይፋ አደረጉ፡፡ የሐማስ ተደራዳሪዎች በኳታር እና ግብጽ ባለሥልጣናት በኩል “እየመከሩበት ነው” የተባለው ይህ እቅድ፤ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኅን ዐቢይ ርእስ ሆኗል፡፡ 

በዕቅዱ ተስማምተዋል ላሏቸው ኔታንያሁ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ መሪዎች፣ ቱርክ፣ ኢንዶኔዥያ እና ለአውሮፓ ሀገሮች ምሥጋና አቅርበዋል። “ትናንት ከሰዓት ከአጋሮቻችን ጋር በሥፋት መክረንበታል” ባሉት እቅድ፤ የዐረብ እና የሙስሊም ሀገሮች፤ “የሐማስን እና የሌሎች የሽብር ድርጅቶችን ወታደራዊ አቅም በማዳከም ጋዛን ከወታደር ነጻ ቀጣና ለማድረግ ቃል ገብተዋል” ብለዋል። “ከሐማስ ጋር ለመግባባት ከሀገሮቹ ጋር ተማምነናል። ሐማስም ይህን ማድረግ እንደሚፈልግ ሰምቻለሁ፤ ይህ መልካም ነገር ነው” ሲሉ አክለዋል።

ከዚህ ጋር አያይዘው የጠቀሱት “አሸባሪ” ሲሉ የጠሩትን የሐማስን መሠረተ ልማት ሁሉ ማውደምን ነው። “ዋሻዎችን፣ የጦር መሣሪያዎችን እና በርካታ የማምረቻ ተቋማትን እያወደምን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። በተጨማሪም “አሁን እየተወያየን ባለንባቸው አካባቢዎች በተለይም በጋዛ እና በዙሪያዋ ከአዲሱ የሽግግር አስተዳደር ጋር በመተባበር የአካባቢ ፖሊስ ኃይሎችን እናሠለጥናለን” ያሉት ትራምፕ፤ ከሐማስ ጋር በሚኖረው ድርድር የዐረብ እና ሙስሊም ሀገሮች ሚናም አፅንዖት በመስጠት የትብብርን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል።

በእቅዱ መሠረት፤ ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር ግንኙነት የሌለው “ቴክኖክራቲክ” የፍልስጤም አመራር ከጦርነቱ ማብቂያ በኋላ የገዛን አስተዳደር ይረከባል። ነገር ግን ይህ የፍልስጤም አመራር የሚመረጠው በመሬቱ ባለቤት በፍልስጤም ሕዝብ ሳይሆን፤ የሰላም እቅዱን ተግባራዊነት በሚቆጣጠር አዲስ ዓለም አቀፍ አካል ነው። ትራምፕ “የሰላም ቦርድ” ሲሉ የጠሩት ይህ አካል፤ ስምምነቱ እንዲሳካ የማድረግና ቁልፍ የቀጣናው እንዲሁም ዓለም አቀፍ መሪዎችን የማሰባሰብ ኃላፊነት እንደሚሰጠው ተናግረዋል። የቁጥጥር አካሉ ሊቀመንበር ራሳቸው እንደሚሆኑም ተናግረዋል። ይህን ይፋ ሲያደርጉ የራሳቸውን ሙሉ ሥም ጠርተው “አለቃው” እርሱ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡  

ትራምፕ ራሳቸው በሚመሩት ቦርድ ሌሎች መሪዎችም እንደሚካተቱ ጠቁመዋል፡፡ “በተገቢው መንገድ እናከናውናለን፡፡ ቦርድ ይኖረናል። በቦርዱ ውስጥ መካተት ከሚፈልጉ ሰዎች መካከል አንደኛው የእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ናቸው። በጣም ጥሩ ሰው [ነው]፤ ሌሎችም አሉ። [ነገር ግን] ሐማስ እና ሌሎች የሽብር ቡድኖች በቦርዱ ውስጥ ምንም ሚና አይኖራቸውም” ብለዋል።

በትራምፕ የተጠቀሱት ብሌር እ.አ.አ ከ1997 እስከ 2007 እንግሊዝን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርተዋል፡፡ እንደ እስራኤል ጋዜጦች ዘገባ ከሆነ፤ ብሌር ከትራምፕ አማች ከጃሬድ ኩሽነር ጋር ለወራት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት ፎር ግሎባል ቼንጅ ከጦርነቱ በኋላ እቅድ እንዲያወጣ በኩሽነር በጀት ተመድቦለት ኃላፊነቱን ወስዷል። ኩሽነር በትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን ከፍተኛ አማካሪ የነበሩ ሲሆን፤ በቅርቡም ለትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በገዛ ጉዳይ አማካሪ ሆነው እየሠሩ ነው፡፡

ትራምፕ ያቀረቡት እቅድ አሜሪካ እና ዐረብ እና ሌሎች አጋሮቿ የገዛን ደኅንነት የሚቆጣጠር International stabilisation force (ISF) በመባል የሚጠራ ዓለም አቀፍ ኅይል እንደሚኖር ይገልጻል፡፡ ይህ ኃይል የረዥም ጊዜ የውስጥ ደኅንነት ለማስፈን መፍትሄ ሰጪ እንደሚሆን ተጠቁሟል። አይኤስኤፍ ከግብፅ እና ከእስራኤል ጋር በመሆን የድንበር አካባቢዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ያግዛል፡፡ ይህ ቡድን ከአዲስ ከሰለጠኑ የፍልስጤም የፖሊስ ኃይሎች ጋር የሚሠራ ነው፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ሐማስ ዛሬ ያቀረብነውን እቅድ መቀበል ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በርግጥ ሐማስ ቀድሞ የነበረው ቁመና ላይ አይገኝም፤ ምክንያቱም ከ20 ሺሕ በላይ ሰዎች ተገድለውበታል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በገዛ የሚገኙ የሐማስ መሪዎች ተቀባይ ሀገር የሚያገኙ ከሆነ ለቀው መውጣት ይችላሉ ተብሏል፡፡

ትራምፕ እቀዱን ካቀረቡ በኋላ መግለጫ ያወጣው የፍልስጤም አስተዳደር፤ ጦርነት ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት በማድነቅ በትራምፕ ላይ ያለውን መተማመን ገልጿል፡፡ ግብፅ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ዮርዳኖስ፣ ፓኪስታን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ “ትራምፕ በገዛ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም ለሚያደርጉት ጥረት” በተመሳሳይ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ሀገሮች መካከል ባለፈው ሳምንት ከትራምፕ ጋር በዋይት ሀውስ የተገናኙት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን፤ “የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በገዛ የሚካሄደውን ደም መፋሰስ ለማስቆም እና የተኩስ አቁም ለማስፈን ያደረጉትን ጥረት እና አመራር አደንቃለሁ” ያሉበትን የተናጥል መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ህንድ፣ ዩኬ፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ኔዝርላንድስ፣ ኦስትሪያ እና የአውሮፓ ካውንስል እቅዱን ደግፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሐማስ እስካሁን ምላሹን አላሳወቀም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

(የዚህ ጥንቅር ዋንኛ ምንጭ አልጀዚራ ሲሆን፣ ሚድል ኢስት ዐይ እና ሐአሬትዝ ተካተዋል)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular