ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ለውይይት ከተቀመጡ የሙስሊም እና ዐረብ መሪዎች መካከል የነበሩት የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን፤ ማክሰኞ ምሽት የፎክስ ኒውስ ጋዜጠኞች አግኝተው “ስብሰባው እንዴት ነበር?” ብለው ሲጠይቋቸው “ፍሬያማ፣ የሚያረካ እና ውጤቱም ጠቃሚ [ሊሆን የሚችል]” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ውይይቱን “ፍሬያማ ነበር” ቢሉትም ዝርዝሩን ከማብራራት ተቆጥበዋል። በአንፃሩ የአሜሪካው ዲጂታል ጋዜጣ ፖለቲኮ አምስት ጋዜጠኞች በስብሰባው ላይ የተገኙ ስድስት ምንጮችን ጠቅሰው ባዘጋጁት ዘለግ ያለ ሪፖርት፣ የስብሰባው ተሣታፊ መሪዎች በተለይ ትራምፕ በጋዛ ዕውቅና ዙሪያ ተቃውሞ በማሰማታቸው “ብስጭታቸውን ሲገልጹ” ነበር ብለዋል። ትራምፕ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በማራቶን በመሰሉት የ55 ደቂቃ ንግግር ወቅትም ፈረንሣይ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በዚህ ሠሞን ዕውቅና የሰጡ ሀገሮች ‘ሐማስን ሸልመዋል’ ሲሉ ውሳኔያቸውን አብጠውጥለውታል።
ዕውቅናውን በአደባባይ ቢያጣጥሉም በተናጠል በተደረገው ውይይት ትራምፕ ለሙስሊም መሪዎች በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንማሁ ቀኝ ዘመም ደጋፊዎች እየተቀነቀነ የሚገኘውን “የፍልስጤምን ግዛቶች በግዳጅ መያዝን” በተመለከተ “ኔታንያሁ እንዲያደርገው አልፈቅድለትም” ማለታቸውን ፖለቲኮ አስነብቧል። ኤርዶጋን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለዚህ ጉዳይ አላነሱም። ብስጭታቸውን ገልፀዋል የተባሉ መሪዎችን አስተያየትም አላስተጋቡም።
ትራምፕ እና ኤርዶጋን ከሌሎች ጋር ባንድነት ካደረጉት ውይይት በኋላ በዋይት ሐውስ ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸው ተሰምቷል። ለዚህ ሲባል የቱርኩ ፕሬዝዳንት ዋሺንግተን ዲሲ መድረሳቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል። ትራምፕ ኤርዶጋንን በዋይት ሐውስ የሚያስተናግዱት ዛሬ ሐሙስ ነው። የዜና ምንጩ ውይይቱ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና በመከላከያ ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ላይ እንደሚተኩር ገልጿል። ኤርዶጋንም ውይይቱን በተመለከተ ሲናገሩ፣ “ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር የምናደርገው ስብሰባ በቀጣናችን ውስጥ የተከሰቱ ጦርነቶችን እና ግጭቶችን ለማስቆም አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት አምናለሁ” ብለዋል።
ትራምፕ የቱርኩን አቻቸውን ተቀብለው ወደ ሀገራቸው ከሸኙ በኋላ፤ የፊታችን ሰኞ ቤንያሚን ኔታንያሁን በተመሣሣይ በዋይት ሐውስ ለመቀበል ቀጠሮ ይዘዋል። በዚህ ቀጠሮ ፕሬዝዳንቱ ይበልጥ ግፊት በማሳደር ቢያንስ 64 ሺሕ ንጹሐንን የቀጠፈውን “የጋዛን እልቂት ያስቆሙ ይሆን ወይ?” የሚለውን ሙስሊም እና ዐረብ መሪዎች መጠበቃቸው አይቀርም። (ሚንበር ቲቪ)












