ከሁለት ሣምንት በፊት ጳጉሜን 4/2017 ከፈጅር ሰላት በኋላ በማዕከላዊ ፓሪስ በሚገኘው ዣቬል መስጅድ ምዕመናን ያጋጠማቸው ክስተት በመዲናዋ ነዋሪዎች ላይ ድንጋጤ ፈጥሮ አልፏል፡፡ ምእመናን በመስጂዱ ደጃፍ ላይ ተጥሎ ያገኙት የአሳማ ራስ ነው፡፡ ለሞንድ የተሠኘው የሀገሪቱ እለታዊ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ በአሳማው ራስ ላይ በሰማያዊ ቀለም “ማክሮን” የሚል ጽሑፍ አርፎበታል፡፡
ከቱር ኤፌል (ኤፊል ታዎር) ሁለት ኪሎ ሜትር ብቻ ርቆ የሚገኘው መስጅድ፤ መሠረታቸውን ከተለያዩ ሀገሮች ያደረጉ ምእመናን ይሰግዱበታል፡፡ በዚያ አልጄሪያውያንም፣ ኢራናውያንም፣ ሊባኖሳውያንና ሌሎችም ለሰላት ይሰባሰባሉ፡፡
ጉዳዩ ቀድሞ ሪፖርት የተደረገላቸው የመስጀዱ አስተዳዳሪና የፓሪስ ሙስሊም ማኅበራት ማስተባበሪያ ፕሬዚዳንት ነጃት ቤናሊ፤ በማለዳ የደረሳቸውን ሪፖርት ለጋዜጠኞች ሲገልጹ “አስደንጋጭ” ነው ብለውታል፡፡ አስደንጋጭ ያሉት ድርጊት በዣቬል መስጅድ ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በዚያው ማለዳ በዋና ከተማዋ ከሚገኙ ሌሎች መስጅድ መሪዎች ሦስት ተጨማሪ የስልክ ጥሪዎችን ሲቀበሉ፤ ሁሉም ጥሪዎች ተመሳሳይ መልእክት ነበራቸው፡፡ ነጃት፤ “እንዲህ ያለ ነገር በእኛ ላይ ሲደርስ ይህ የመጀመርያችን ነው” ብለዋል፡፡
የፓሪስ አቃቤ ሕግ እንደገለጸው፤ በእለቱ ማለዳ ላይ በአጠቃላይ በዘጠኝ መስጀዶች ላይ (አራት በፈረንሳይ ዋና ከተማ እና አምስት በከተማ ዳርቻዎች) ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ ያስታወቀው የወንጀል ምርመራ መምሪያው፤ ድርጊቱን የያዘው “በዘር፣ በዜግነት ወይም በሃይማኖት ላይ በመመርኮዝ ለጥላቻ ወይም ለዓመፅ በአደባባይ ማነሳሳት” በሚል መዝገብ ነው፡፡
መምሪያው እስካሁን ድረስ በደረሰበት የምርመራ ሒደት፤ ድርጊቱ ከመፈጸሙ አንድ ቀን በፊት፤ የሰርቢያ ሰሌዳ የለጠፈ ተሸከርካሪ እያበርሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በሰሜናዊው የኖርማንዲ ክልል ወደሚገኝ አንድ ገበሬ ጋር ደርሰው “10 ገደማ” የአሳማ ራስ መግዛታቸውን አስታውቋል፡፡ በፓሪስ ኦበርካምፕፍ ሰፈር ደርሰው ከዘጠኙ መስጊዶች ፊት ለፊት የአሳማዎቹን ራስ ካስቀመጡ በኋላ ተሽከርካሪው በዚያኑ ቀን ማለዳ ከፈረንሳይ ወደ ቤልጂየም ድንበር ማቋረጡን በደኅንነት ካሜራ መረጋገጡን አክሏል።
የፓሪስ አቃቤ ሕግ ቢሮ ድርጊቱን “በሀገር ውስጥ ብጥብጥ በመፍጠር ዓላማ በተንቀሳቀሱና በአፋጣኝ ከሀገር በወጡ የውጭ ዜጎች የተፈጸመ” መሆኑን ለመገናኛ ብዙኅን ገልጿል፡፡ ዓላማው “የዜጎቻችንን ህሊና ለመበረዝ፣ በመጨረሻም ስለምንኖርበት ሀገር፣ ስለደኅንነታቸው ጥያቄ እንዲያነሱና በማኅበረሰቦች መካከል መከፋፈልን ለመፍጠር ነው” ሲሉ የፓሪስ አቃቤ ሕግ ሎሬ ቤኩዋ ተናግረዋል።
በማዕከላዊ ፓሪስ በሚገኘው ዣቬል መስጅድ የአሳማ ራስ ተጥሎ መገኘቱን ተከትሎ የመስጅዱ አስተዳዳሪ ነጃት፤ በመዲናዋ የሚገኙ የሌሎች ቤተ እምነት መሪዎች አነጋግረውኛል ብለዋል፡፡ መሪዎቹ ጥቃቱን “በሙስሊሞች ላይ ብቻ የተፈጸመ አድርገን አንወስደውም፤ እርስ በእርስ ሊያጋጩን ፈልገው ያደረጉት ነው” ማለታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህ ክስተት የተሰማው በፈረንሳይ በሙስሊሞች ላይ የሚፈጸሙ የጥላቻ ወንጀሎች እየጨመሩ ባሉበት ወቅት ነው። በፈረንሳይ በ2025 የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ውስጥ 145 ሙስሊሞች ላይ ያነጣጥሩ የጥላቻ ድርጊቶች ተመዝግበዋል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በ75 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በቅርብ ጊዜ ብቻ በመስጅዶች የእሳት ቃጠሎ ሙከራ፣ ማስፈራሪያዎች እና አቡበከር ሲሴ በተባለ ወጣት ግድያዎችም ተፈጽመዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












