የኢትዮጵያ ሲቪል ሠርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወስደው የማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። ሚኒስቴሩ ይህን የገለፀው የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ሀገር አቀፍ ፈተና ወስደው የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ያመጡ ለትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ በሆኑ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች በወጪ መጋራት (ስኮላርሽፕ) ለመማር ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ባደረገው ጥሪ ነው።
ዛሬ ሰኞ መስከረም 12/2017 ባወጣው መግለጫ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ እና የትምህርት መስክ ምርጫቸውን በየትምህርት ቤታቸው በተወከሉ መምህራን በኩል እስከ መስከረም 14/2018 ድረስ ማስተካከል እንደሚችሉ የገለፀው ትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከ2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎችን ስለሚቀበል “ተማሪዎች ምርጫቸው ውስጥ ማካተት እንደሚችሉ” ጠቁሟል። በዚህ ምርጫ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና አዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች እንደማይካተቱ ተገልጿል።
የሀገሪቱን የሲቪል ሠርቪስ አቅም ለማጎልበት በሚል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ ሪፎርም ለማድረግ ጥናት እያካሄደ የሚገኝ ተቋም ነው። ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያሣየው፣ እያካሄደ የሚገኘው ሪፎርም የጥናት ውጤት ዩኒቨርሲቲው የወደፊት አቅጣጫ ምን መምሰል እንዳለበትና የሚመራበትም የህግ ማዕቀፍ የሚያሳይ ዝርዝር ጉዳዮችን ባካተተ መልኩ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ነው።
በጥናቱ ውጤት እንደተመላከተውም የዩኒቨርሲቲው Public Service and Governance University በሚል ሥያሜ ቀደም ሲል እንደነበረው ለትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ በመሆን ይቀጥላል። በመሠረታዊነት ሀገራዊ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ሪፎርሙን የሚያግዝ ጠንካራ ሲቪል ሰርቫንት የማፍራት፣ የትኩረት አቅጫውን በፐብሊክ ሰርቪስ ላይ ያደረገ፣ በማህበራዊ ሳይንስ እና ዲቨሎፕመንት ስተዲስ፣ ፐብሊክ ሴክተር ቢዚንስ እና ምጣኔ ሀብት እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን እና በፐብሊክ ሰርቪስ ኢኖቬሽን በትኩረት እንደሚሠራም ተጠቁሟል። (ሚንበር ቲቪ)












